የተመድ ቃል አቀባይ ዕለታዊ ገለጻ

  • ቪኦኤ ዜና

ስቴፋን ዱጃሪች

በኢትዮጵያ የአፋር ክልል ፈንቲ ወረዳ ጋላኮማ ቀበሌ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው አንድ ትምህርት ቤት እና የጤና ጣቢያ በተፈናቃዮች ላይ ስለተፈጸመ ጥቃት እና በመጋዘን ላይ ስለተፈጸመ ዝርፊያ የቀረበውን መረጃ ሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ኦቻ የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ተናገሩ።

ስቴፋን ዱጃሪች በዕለታዊ ጋዜጣዊ ጉባዔአቸው በትግራይ ክልል እሳቸው የትግራዩ ግጭት ወደአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች መስፋፋቱን አመልክተዋል። አስከትለው በሪፖርቶች መሰረት እርሳቸው "የትግራይ ኃይሎች" ሲሉ የጠሯቸው እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አሸባሪው ብሎ የፈረጀው ህወሓት ሃይሎች ወደአማራ ክልል እና አፋር ክልል መዝለቃቸውን ተከትሎ በአማራ ክልል ሁለት መቶ ሽህ በአፋር ክልል ከሰባ ስድስት ሽህ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል።

በአፋር ክልል ፈንቲ ዞን ግላኮማ ቀበሌ ተፈናቃዮችን ባስጠለሉ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ ስለተካሄደ ጥቃት እና በመጋዘን ላይ የተፈጸመ ዝርፊያ ውድመት መድረሱን የገለጹ መረጃዎችን ኦቻ እየተከታተለ ይገኛል ብለዋል።

የአፋር ብሄራዊ ምክር ቤት በጋላኮማ የተፈናቃዮች መጠለያ ሳሉ በህወሓት ጥቃት ህይወታቸውን እንዳጡ ለገለጻቸው ከሁለት መቶ በላይ ተፈናቃዮች ትናንት የሦስት ቀን የሃዘን ወቅት ማወጁ እንዲሁም በጥቃቱ የቆሰሉ ከአርባ የሚበልጡ ሰዎች ዱብቲ ሆስፒታል ህክምና ላይ መሆናቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

ትግራይ ውስጥ የሰብዓዊ ረድኤት ተደራሽነት ሁኔታው በእጅጉ እንደተሽሽለ የገለጹት ቃል አቀባይ ዱጃሪች በአሁኑ ሰዓት የክልሉን ሰባ አምስት ከመቶ አካባቢ ለመድረስ ችለናል ብለው ሆኖም የሰብዓዊ አቅርቦት ወደክልሉ የመግባት ሁኔታው አሁንም በቂ አይደለም ነው ያሉት።

በአፋር በኩል ያለው ብቸኛው የእርዳታ አቅርቦት መስመር በጸጥታ መደፍረስ በየቦታው ባለው ፍተሻ ምክንያት በተሟላ ሁኔታ የሚያሳልፍ እንዳልሆነ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የአየር መንገድ አገልግሎት በዕቅዱ መሰረት ከአዲስ አበባ ወደመቀሌ በረራ ማሄዱን እና ከመቀሌ ወደሰመራ የድርጅቱን ሰራተኞች ማጓጓዧ መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "ኦነግ ሸኔ" ብለው የሚጠሩት እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ጦር" ብሎ የሚጠራው ቡድን መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ህወሓት ጋር ወታደራዊ ጥምረት መስርቻለሁ ብሎ ማስታወቁ ላይ የመንግሥታቱን ድርጅት መልስ የተጠየቁት ቃል አቀባይ "ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ ይኖራል ብለን አናምንም" ብለዋል።

"ትግራይ ውስጥ ግጭቱ ጋብ ብሎ ሰብዓዊ እርዳታ በተሻለ ለማድረስ የተቻለም ቢሆን ግጭቱ በአንዳንድ ዞኖች ቀጥሏል። እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ ጥሰት መድረሱን የሚናገሩ ሪፖርቶች እየተመለከትን ነን" ያሉት ዱጃሪች "አምነስቲ ኢንተርናሻናል ትግራይ ውስጥ በሴቶች ላይ በወታደራዊ ኃይሎች ተፈጽሟል የተባሉ የመድፈርና በባርነት የመያዝ ጥቃቶችን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት እጠቅሳለሁ" ካሉ በኋላ "ስለሆነም የግጭቱ መቀጠል በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ዘግናኝ ስቃይ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው" ብለዋል።