የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በሚያደርገው ስብሰባ በዩክሬን በተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስብሰባው የሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀል ሊከሰሱ ይገባል” ብለው በተናገሩ ማግስት ነው፡፡
የማክሰኞ የምክር ቤቱ ስብሰባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዥ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርትን ግሪፍትስ እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ንግግር ያሰሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዚህን ወር የምክርቤቱን ተረኛ ፕሬዚዳንትነት የያዘችው እንግሊዝ መሆኗ ተገልጿል፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅት የእንግሊዝ አምባሳደር ባርባራ ዎድዎርድ “በሩሲያ ወረራ በዩክሬን የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ጉዳይ የስብሰባው ቀዳሚና ማዕከል መነጋገሪያ ይሆናል” ሲሉ ለጋዜጠኞ ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ ትናንት ሰኞ ረፋዱ ላይ ጉዳዮን ከጉተሬዥ ጋር ተነጋግረውበታል፡፡ ንግግሩ በዩክሬን መዲና ዙሪያ በምትገኘው ቡቻ በሩሲያ ወታደሮች ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውና በቅርብ ቀናት ይፋ የተደረገው ግፍን እንደሚጨምርም ተመልክቷል፡፡
ኩሌባ ባስተላለፉት የትዊት መልክዕክትም “ዩክሬን የሩሲያን የጦር ወንጀሎች በማሳየት ተጠያቂ ለማድረግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያሉትን ሁሉንም አማራጮች አሟጣ የምትጠቀም መሆኑን አጽንኦት ተሰጥቷል” ብለዋል፡፡
ሞስኮ በቡቻ ተደርጓል የተባለውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ ክስ አስተባብላለች፡፡ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ ጉዳዩ “የጸረ ሩሲያ ተቃውሞን ለመቀስቀስ የተቀነባበረ ትርኢት ነው” ብለውታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ አምባሳደርም በበኩላቸው በማክሰኞው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እውነታውን የሚያሳይ መረጃ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
የማክሳር ቴክኖሎጂ ሳተላይት ድርጅት ቃል አቀባይ፣ ትናንት ሰኞ ባሰጡት መግለጫ፣ ባላፈው መጋቢት አጋማሽ ወር ውስጥ፣ ክበቡቻ የተሰበሰቡት ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ በቅርቡ በየጎዳናው ላይ ተዘርግተው ለሳምንታት በግልጽ ይታዩ ከነበሩት አስክሬኖች ፎቶግራፍና የቪዲዮ ምስሎች ጋር የሚመሳሰሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ እንዳስታወቀው የዩክሬን ኃይሎች በቸርኒቭ እና በሰሜን ኪየቭ የነበሩ የሩሲያ ኃይሎች እንዲያፈግፍጉ በማድረግ በሰሜን ዩክሬን ያሉ አካባቢዎችን መልሰው ተቆጣጥረዋል፡፡
መግለጫው አክሎ እንዳስታወቀው የሩሲያ ኃይሎች ከዚህ በኋላ በምስራቅ ዩክሬን መልሰው ለመዋጋት ከፈለጉ ራሳቸውን እንደገና በሚገባ መልሰው ማደራጀት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የዩክሬን ኤታማዦር ሹም የሩሲያ ኃይሎች ትኩረታቸውን ማድረግ የሚፈልጉት በዶንቴስክ እና ሉዋንስክ ግዛቶች ሲሆን፣ ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡