በኢትዮጵያ ለሰላም የተሻለ ተስፋ እንዳለ የመንግሥታቱ ድርጅት ገለፀ

  • መለስካቸው አምሃ

Your browser doesn’t support HTML5

በኢትዮጵያ ለሰላም የተሻለ ተስፋ እንዳለ የመንግሥታቱ ድርጅት ገለፀ

በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቶች መቀነሳቸውንና ለሰላምም የተሻለ ዕድል እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ተናገሩ። ብሔራዊ ምክክሩን ለመጀመርና የሰላሙን መንገድ ለማፈላለግ ግጭቶች መቆም እንደሚገባቸውም ገለፁ።

ምክትል ዋና ጸሐፊዋ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ሲመለሱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት አጭር መግለጫ፤ በግጭቱ ማንም አሸናፊ እንደማይሆንና የግጭቱን አሳዛኝ ገፅታ እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በሕዝቡና በመንግሥት በኩል ለሰላም የሚደረገውን ጥረት እንዳስተዋሉ ገልፀዋል። በጎበኟቸው አካባቢዎችም ከመሪዎችና ከሕዝቡ ጋር ስለወደፊቱ ተስፋዎችና ሰላምን ስለማምጣትም እንዴት ያለ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ማነጋገራቸውን የገለፁት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ በሃገሪቱ ለሰላም የተሻለ ተስፋ እንዳለ አመላክተዋል።

“ከዚህ መንግሥት ጋር ከሚነጋገሩት የአፍሪካ መሪዎች እና የእኛ መሪዎች ጋር እንነጋገራለን። ዛሬም የመስክ ጉብኝት ሳደርግ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አፋር ነበሩ። ትናንት ደግሞ ትግራይ ነበሩ። እና ንግግሮቹ እየቀጠሉ ናቸው። ግጭቶቹ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበሩት ዛሬ የቀነሱ መሆናቸው አይጠረጠርም። በተሻለ ሁኔታ እንገኛለን። በብሄራዊ ምክክሩ ዙሪያ እና ሰላምን በማፈላለጉ ረገድ ዛሬ ብዙ የተሻለ ውይይት እና ንግግር አለ።” ብለዋል።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አሚና መሐመድ በዚህ ጉብኝታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ከኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር የእርዳታ ቁሳቁሶችን በእጅጉ ለሚያስፈልጓቸው ሰዎች ሲያድሉ እንዳገኟቸውም ተናግረዋል።

የሰብዓዊ እርዳታው ዘግይቶ የደረሰ መሆኑን የጠቆሙት አሚና ትልቁ የድርጅታቸው ተልኮ እንደሆነም አስገንዝበዋል። በተለይ በዚህ ግጭት ምክኒያት በተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ በጣም የተጎዱት ሴቶች መሆናቸውንም አስታውሰው የእርዳታውን አጣዳፊነትም በአፅንኦት አንስተዋል።

ጉዟቸውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሰላምን ለማፈላለግ የተደረገ የትብብርና አጋርነት ጉዞ እንደነበረ ገልፀዋል።

“አስቀድማችሁ እንደሰማችሁት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ በሀገሪቱ ውስጥ ግጭቶች እንዲቆሙ ደጋግመው ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ መንገድ ነው ሰላምን ማፈላለግ የምንችለው። ይህ ጉዞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለንን ሕብረት እና አጋርነት የገለፅንበት ጉዞ ነበር።

ለዚህ ሰላም ሕዝቡ መንገድ እንደሚያገኝለትም እምነት አለን። የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ እዛ እንዲደርስም፣ አብረነው እንጓዛለን። ከዛ በኋላ ነው ስለልማት መነጋገር የምንችለው። ይሄ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጉዞ ዋናው ቁም ነገር ነው።”

የመንግሥታቱ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ የተገኙት በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዋና ጸሐፊውን አንቶኒዮ ጉተሬዥን ወክለው ለመገኘት ነው።

በጉባኤው ከተሳተፉም በኋላ ወደ አማራ፣ ትግራይ፣ ሶማሌና አፋር ክልል ጉብኘት አድርገዋል።