ሩስያ ዩክሬን ውስጥ በምታካሂዳቸው ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ በቂ እርምጃ አልወሰደችም ሲሉ የ ተ መ ድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ተናገሩ፡፡
ቮልከር ትርክ ዛሬ እንዳስታወቁት ሩሲያ እ አ አ ባለፈው 2022 ዓመተ ምሕረት የካቲት ላይ ወረራዋን ከከፈተችበት ጊዜ ወዲህ 10 ሺህ ሲቪሎች መገደላቸውን ጽህፈት ቤታቸው አረጋግጧል፡፡ የተገደሉት ሲቪሎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊበልጥ እንደሚችል አክለዋል፡፡
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን አካባቢዎች በዘፈቀደ የታሰሩ እና ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች መኖራቸውን ቢሮአቸው መመዝገቡን የገለጹት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነሩ የኮሚሽኑ ሠራተኞች የጦር ምርኮኞች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ለመግባት እንዳልቻሉም አስረድተዋል፡፡
ሩስያ መዲና ሞስኮ አየር ክልል ውስጥ በመብረር ላይ የነበረ ሰው አልባ አይሮፕላን ( ድሮን) በአየር መከላከያዎቻችን ተመትቶ ወድቋል ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ ተናገሩ፡፡
የዩክሬን የጦር ኃይል በበኩሉ ትናንት ሌሊት ሁለት ድሮኖች መትቶ እንደጣለ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮሎና እና የብሪታኒያ አቻቸው ዴቪድ ካምረን ፓሪስ ላይ ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ሁለቱ ሀገሮች ለዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የሩስያ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት የአውሮፓ ሕብረት ለሚጥልብን አዲስ ዙር ማዕቀብ ተዘጋጅተናል ሲል ተናገረ፡፡ የአውሮፓ ሕብረት
ምክር ቤት ትናንት ሰኞ ያጸደቀው ማዕቀብ የሩስያ አልማዝ ወጪ እና ገቢ ንግድ ላይም ያነጣጠረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡