በአምስቱ የፀጥታ ምክር ቤቱ ቋሚ አባላት የተያዘው ሥልጣን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሊያፈራርሰው ነው ሲሉ ተሰናባቹ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር አስጠነቀቁ።
በዚህ የአውሮፓውያን ወር መጨረሻ ሥራቸውን ለመልቀቅ እየተሰናዱ ያሉት ዘይድ አል ሁሴን ይህን ያሉት ጂኔቫ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ነው።
ድምፅን የመሻር ሥልጣን ያላቸው አምስቱ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩስያና ዩናይትድ ስቴትስ አብዛኛውን ጉዳይ የሚመሩት እነሱ ናቸው አጣብቂኞችም እየፈጠሩ ነው ሲሉ ዘይድ ራአድ አል ሁሴን አማርረዋል።
ተሰናባቹ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር በመቀጠል ድምፅ በመሻር ሥልጣን የተጣሉትን ሶሪያን እና የእስራኤልን የፍልስጥኤም ፖሊሲ አስታውሰው ሲናገሩ እነሱ ሲተባበሩ ጉዳዮች ይንቀሳቀሳሉ ሳይተባበሩ ሲቀሩ ደግሞ ሁሉ ነገር ባለበት ይቆማል። በአጠቃላይም ድርጅቱ ወደ ዳር የሚገፋበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
በዓለም ዙሪያ እየተቀጣጠለ የመጣውን ብሄርተኝነት በተዘዋዋሪ በመጥቀስ ሲናገሩም የሰው ልጅ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተማርነውን እየዘነጋው ሳይሆን ኣልቀረም ብለዋል። ከነዚያ ታሪካዊ የክፉ ጊዜ ተመክሮዎች እየራቅን በመጣን ቁጥር ያ ቀን እንዳይደገም ለመከላከል የተፈጠሩትን ተቋማት እንደፈለገን መጫወቻ ወደማድረጉ እንሄዳለን ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ዮርዳኖሳዊው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ሹም አል ሁሴን ለተጨማሪ የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን ለመቀጠል ፈቃደኛ አልሆኑም ። የቀድሞዋ የቺሌ ፕሬዚደንት ሚሼል ባርትሌት ይተኳቸዋል።