የጋዛ ውጊያ ተስፋፍቶ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው ጉቴሬዝ አስታወቁ

  • ቪኦኤ ዜና

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ የእስራኤል እና የሐማስ ውጊያ መልሶ መቀጠሉ እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን ትናንት ሰኞ ተናገሩ፡፡ ሐማስ እስራኤል ላይ ሮኬት መተኮሱ እስራኤልም የአየር ድብደባዎቿን እና የየብስ ጥቃቷን ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ ዘልቃ መቀጠሏ ያሰጋቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ባወጡት መግለጫ “የእስራኤል ኃይሎች ያለውን እጅግ አስከፊ ሰብዓዊ ችግር የሚያባብስ ድርጊት ከመፈጸም እንድትቆጠብ እና ሲቪሉን ህዝብ ከባሰ ስቃይ እንድትታደግ ተመድ ማሳሰቡን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

ሁሉም ወገኖች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ረድኤት ህግጋት መሠረት ያለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ የጠየቁት ጉቴሬዥ ጋዛ ውስጥ ለሰብዐዊ ዕርዳታ የሚያስፈልገው የተኩስ ማቆም ፋታ እንዲቀጥል ተማጽነዋል፡፡ በተጨማሪም አሁንም በሐማስ እጅ ያሉት ታጋቾች በሙሉ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ዋና ጸሐፊው አሳስበዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ትናንት ሰኞ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ባካሄደው ስብሰባ የሰብዐዊ ረድዔት የተኩስ ፋታው መፍረሱ እና ውጊያው መቀጠሉን በሚመለከት ተነጋግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል እና በርካታ የአይሁዶች ድርጅቶች እአአ ጥቅምት 7 ቀን ሐማስ በሴቶች ላይ “አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ፈጽሟል” ስላሉት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአመዛኙ በቸልታ ተመልክቶታል ስላሉት ጥቃት አጉልተው ለመናገር ትናንት ሰኞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዝግጅት አካሂደዋል፡፡