የተመድ የደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ተልዕኮውን ዘመን አራዘመ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ቡድን በደቡብ ሱዳን በቦር ጆንግሌ ግዛት ውስጥ ቦር ካምፕ ለተፈናቃዮች ጥበቃ ሲያደርግ እአአ ሚያዚያ 29/2014

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት በሰጠው ድምፅ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮው ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል ፈቀደ። ሩስያ እና ቻይና ድምፅ ተአቅቦ ያደረጉ ሲሆን የተቀሩት አስራ ሦስቱ የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔውን ደግፈዋል።

በዚህም መሰረት የሰላም ጥበቃ ተልዕኮው አንሚስ አሁን ባለው የሰራዊት መጠኑ ለአንድ ዓመት እንዲቀጥል ተወስኗል።

ቻይና ቀደም ብላ ውሳኔውን እንደምትደግፍ ፍንጭ ከሰጠች በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በውሳኔው ሰነድ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንዲካተት አጥብቃ መጠየቋን ተከትሎ ሃሳቧን ቀይራለች።

በመንግሥታቱ ድርጅት የቻይና ምክትል ተወካይ ዳይ ቢንግ የውሳኔ ሰነዱን በእጅጉ ሚዛናዊነት የጎደለው ያሉ ሲሆን የሩስያ አምባሳደር አና ኤቪስቲኚቫ ደግፈው ሞስኮ ያቀረበችው ማሻሻያ አለመካተቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።