የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሦሪያውያን ሰብአዊ ርዳታ ለማስገባት ተስፋ እንዳለው የድርጅቱ ባለሥልጣናት ዛሬ ማክሰኞ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩትን ፕረዝደንት ባሻር አል አሳድን ካስወገዱት አማጺያን ጋራ የሚያደርጉትን ንግግር ቀጥለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ከአማፂያኑ መሪ አህመድ አል ሻራ ጋራ “ገንቢ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸው ይህም “ወሳኝ የኾኑ የሰብአዊ ድጋፎችን መጠን ለማሳደግ የሚያመቻች መሠረት ይሆናል” ብለዋል ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴረዥ፣ በበኩላቸው በሦሪያ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ባሻር የሚመራው መንግሥት የሰብአዊ ረድኤት ሠራተኞችን ለመጠበቅ፣ የሰብአዊ ርዳታ አገልግሎቶች በሁሉም ድንበሮች በኩል እንዲገቡ ለማስቻል እና ለሰብአዊ ረድኤት ሠራተኞች ፈቃድ እና ቪዛ ለማፋጠን የገባውን ቃል በደስታ መቀበላቸውን ተናግረዋል።
በሦሪያ የፈረንሳይ ልዩ መልዕክተኛ ዣን ፍራንሲስ ጊላሜ ዛሬ ማክሰኞ ሦሪያን በጎበኙበት ወቅት "ፈረንሳይ በሽግግራቸው ወቅት ከሶሪያውያን ጋራ ለመኾን በዝግጅት ላይ ነች" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፈረንሳዩ ልዩ መልዕክተኛ ሽግግሩን ከሚመሩት ጋራ ለመወያየት በቅርቡ ወደ ሦሪያ ከሄዱት ልዑካን መካከል አንዱ ናቸው። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዲፕሎማቶቹ በደማስቆ ከአማፂያን መሪዎች ጋራ ዛሬ የመጀመሪያውን ውይይት እንደሚያደርጉ ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካያ ካላስ በበኩላቸው ኅብረቱ ለሶሪያ የሚያደርገውን ሰብአዊ ርዳታ እያጠናከረ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የሦሪያን "የዲሞክራሲ ምኞት" እንዴት እንደሚደግፍ ኅብረቱ እያጤነ መኾኑንም የውጭ ፖሊሲ ኃላፊዋ ተናግረዋል።