ተመድ በኀይል ከሥልጣን የተወገዱት የኒዤር ፕሬዝዳንት ዕጣ አሳስቦኛል አለ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ

በመንፈቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው በተወገዱት የኒዤሩ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙም እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቀጠለው የዘፈቀደ እስር እና ያሉበት “አስከፊ አያያዝ” በእጅጉ እንዳሳሰባቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አስታወቁ።

በዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዥ ስም በንባብ የቀረበው መግለጫ፣ ባዙም፥ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአፋጣኝ እንዲለቀቁና ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ይጠይቃል።

መግለጫውን ያሰሙት የድርጅቱ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ፣ “ባዙም እና ቤተሰባቸው፥ መብራት፣ ውኃ፣ ምግብ እና መድኃኒት በሌለበት የሚገኙበትን ኹኔታ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ያውቃል፤” ብለዋል።

በተመሳሳይ፣ በወታደራዊ ስዒረ መንግሥት ከሥልጣን ተወግደው ላለፉት ሁለት ሳምንታት በቁም እስር ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ባዙም፣ የምግብ አቅርቦት እንደተሟጠጠባቸውና “ይበልጥ እየከፋ በመጣ ኹኔታ ውስጥ” እንዳሉ፣ አንድ አማካሪያቸው ባለፈው ረቡዕ መናገራቸው ተዘግቧል።

መንፈቅለ መንግሥቱን ያካሔደው የኒዤር ወታደራዊ ሁንታ በበኩሉ፣ ጎረቤት ሀገራት፣ “‘ሕግ ለማስከበር” በሚል፣ የትኛውንም ዐይነት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከሞከሩ፣ “ፕሬዚዳንቱን እንገድላቸዋለን” ሲል፣ ለዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች እንደ ዛተ፣ ሁለት ምዕራባውያን ባለሥልጣናት፣ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሀገር ለመምራት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ባዙም፣ ከባለቤታቸው እና ከወንድ ልጃቸው ጋራ፣ ከሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. አንሥቶ፣ በኒያሚ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት፣ በኀይል በያዟቸው ወታደሮች እጅ እንደሚገኙ ይታወቃል።