የዓለም ጤና ድርጅት ተሻሽሎ የተሠራው የኮሌራ መከላከያ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጠ። የክትባቱ መፈቀድ እየተባባሰ ያለውን ወረርሽኝ ለመዋጋት እንደሚረዳ ተነግሮለታል።
በዓለም ላይ ያለው የኮሌራ መከላከያ ክትባት ክምችት እየተሟጠጠ ሲሆን ድሆች ሀገሮች ወረርሺኙን ለመቆጣጠር እየተቸገሩ መሆኑ ተጠቁሟል።
የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት ፈቃድ የሰጠው ክትባት አሁን እየተሰጠ ያለውን ክትባት የሠራው "ኢዩባዮሎጂክስ" ኩባኒያ ሲሆን የተሻሻለው ክትባት ዋጋው ከፊተኛው እንደሚረክስ እና በፍጥነት ሊመረት የሚችል መሆኑ ተመልክቷል።
የዓለም የጤና ድርጅት ፈቃድ በመስጠቱ ጋቪ የተባለውን ጥምረት የመሳሰሉ የክትባት ለጋሽ ድርጅቶች እና የመንግሥታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ዩኒሴፍ ክትባቱን ለድሆች ሀገሮች መግዛት ይችላሉ።
የዩኒሴፍ የአቅርቦት ክፍል ኃላፊ ሊይላ ፓካላ በሰጡት መግለጫ አዲሱ ክትባት የድርጅታቸው አቅርቦት በሀያ አምስት ከመቶ እንደሚያሳድገው አመልክተዋል። ጋቪም ባለፈው እንደ አዎርፓውያን የቀን አቆጣተር 2023ዓ.ም የነበረው የክትባት ክምችት 38 ሚሊዮን እንደነበረ ጠቁሞ በዚህ ዓመት ወደ 50 ሚሊዮን ክትባት ለማከማቸት እንችላለን ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።