ተመድ በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ ማህበረሰብ ተኮር ጥቃቶች እንዳሳሰበው ገለፀ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በኢትዮጵያ ስለሚፈጸሙ ማህበረሰብ ተኮር ሁከቶችና በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቅርብ ቀናት እየወጡ ያሉት ሪፖርቶች በጥልቅ እንዳሳሰቧቸው አስታወቁ።

በጥቃቶቹ ብዛት ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዋና ፀሃፊው ትናንት ባወጡት መግለጫ ጠቅሰው ለተገደሉት ሰዎች ቤተሰቦች ጥልቅ ሃዘኔን እገልጻለሁ ብለዋል። የጥቃቱ አድራሾች ለፍርድ እንዲቀርቡም ዋና ፀሃፊው ጨምረው አሳስበዋል።

አስከትለውም ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች በአስቸኳይ ውጥረቱን የሚያረግቡ ርምጃዎች እንዲወስዱ እና ያሉ ተግዳሮቶች አሳታፊ እና ሰላማዊ በሆነ ንግግር መፍትሄ እንዲፈለግላቸው የተመዱ ዋና ፀሃፊ ተማጽነዋል።