የዩክሬን ጦር ትላንት ሌሊት በሀገሪቱ ማዕከላዊና ምሥራቃዊ ክፍል 47 የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) መትቶ መጣሉን ዛሬ ሐሙስ አስታወቀ።
ሩሲያ ለጥቃት ያሰማራቻቸው በአጠቃላይ 72 ድሮኖች እንደነበሩም የዩክሬን ጦር ተናግሯል።
የዩክሬን አየር መከላከያ ድሮኖቹን መትቶ የጣላቸው በቸርካሲ፣ ቼርኒሂቭ፣ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ካርኪቭ፣ ኬርሰን፣ ኪሮቮራድ፣ ኪየቭ፣ ሚኮላይቭ፣ ፖልታቫ፣ ኦዴሳ እና ሱሚ ክልሎች መሆኑ ተገልጿል።
በአካባቢዎች ያሉ ባለሥልጣናት ከፍተኛ ጉዳት ስለመድረሱ ወዲያውኑ አልገለጹም። የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር 13 የዩክሬን ድሮኖችን በአብዛኛው በዩክሬንና ሩሲያ ድንበር አካባቢዎች መደምሰሱን ዛሬ ሐሙስ ተናግሯል። ድሮኖቹ የተመቱት በብራያንስክ፥ ቤልጎሮድ፥ ኩርስክ፥ ካልጋ እና ቮሮኔዥ ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።
የብራያንስክ እና የካሉጋ ገዥዎች በክልላቸው የተመዘገበ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ውድመት የለም ብለዋል። የሐሙስ ጥቃቶች የደረሱት የሩስያ ወታደሮች ኪቭ ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን የገደሉበትን ጥቃት በፈጸሙ ማግሥት ነው።