በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የኬንያ አየር መንገድ የመለዋወጫ እጥረት ስለገጠመው አንዳንድ በረራዎቹን ሊያቆም ይችላል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈፀሚው ተናግረዋል።
ሮይተርስ ዋና ሥራ አስፈፀሚ የሆኑትን አላን ኪላቩካን ጠቅሶ እንደዘገበው በዩክሬን ያለው ጦርነት የአቅርቦት መዛባት በመፍጠሩ አየር መንገዱ አንዳንድ በረራዎቹን ለመሠረዝ ሊገደድ ይችላል።
ኪላቩካ ጨምረው እንዳሉት አየር መንገዱ የበረራ መስተጓጎል እየገጠመው መሁኑንም ጨምረው ተናግረዋል። ይህም ለጥገና የሚያስፈልጉ መለዋወጫዎች ዘግይተው በመድረሳቸው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዩክሬን ያለው ጦርንት “ከሩሲያ ይገኝ የነበረውንና ለዓለም አየር መንገዶች ወሳኝ የሆነውን የአቅርቦት ስንሰለት ቆላልፎታል” ብለዋል ኪላቩካ።
ከሩሲያ የሚገኘውና የበረራ ኢንዱስትሪው የሚጠቀመው የታይቴኒየም ብረት እጥረትን እንደማሳያ አንስተዋል ኪላቩካ።
የኬንያ አየር መንገድ ቦይንግና ኢምብሬየር አውሮፕላኖችን ለበረራ እንደሚያሰማራና ዋና ዓላማውም ናይሮቢን ማዕከል በማድረግ አፍሪካውያንን ከዓለም፣ የዓለም ተጓዦችን ደግሞ ከአፍሪካ ጋር ማገናኘት እንደሆነ ሪፖርቱ አውስቷል።