ሩሲያ ዩክሬን ላይ አዲስ የሚሳይል ጥቃት አካሄደች

  • ቪኦኤ ዜና

በሮኬት ጥቃት ወቅት ሰዎች ምድር ባቡር ጣቢያ ውስጥ ተሰባስበው፤ ኪየቭ፣ ዩክሬን

ሩሲያ ዛሬ ሌሊት ዩክሬን ላይ በተከታታይ የሚሳይል ጥቃት አድርሳለች፡፡ በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰው መገደሉ ገልጿል፡፡ ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ደግሞ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬናውያኑ ኃይሎች ላይ ጥቃታቸውን እያፋፋሙ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

ሩሲያ ጥቃቱን ያደረሰችው ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የተራቀቁ ታንኮችን ለመላክ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ንግግር ባደረጉ በጥቂት ሰዓታት ተከትሎ ነው፡፡

ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ረጅም ርቀት ተተኳሽ ሚሳይሎች እና የጦር አውሮፕላኖች እንዲለግሱ ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡

የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ኪትቼንኮ በመዲናዋ ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች እንደቆሰሉ ተናግረው ነዋሪዎች ከመጠለያ እንዳይወጡ አሳስበዋል፡፡ “ብዛት ያላቸው ሚሳይሎች መትተን ጥለናል” ሲሉ የከተማዋ ወታደራዊ አስተዳደር ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

በኔቶ አባል ሀገሮች መካከል ወራት የፈጀ ክርክር ከተካሄደ በኋላ በርሊን እና ዋሽንግተን ለዩክሬን ታንኮቹን ሊልኩ ተስማምተዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ 31 እጅግ ዘመናዊ እና የተራቀቁ “አብራምስ” የተባሉ ታንኮችን እንደምትልክ ትናንት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል፡፡

ሞስኮ በበኩሏ ምዕራባውያን ሀገሮች የተራቀቁ ታንኮችን ለዩክሬን መስጠታቸውን “አደገኛ የትንኮሳ ተግባር” ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዋይት ሀውስ በሰጡት ቃል ኔቶ የሚልካቸው ታንኮች ለዩክሬን ኃይሎች “በሜዳ ውጊያ የመንቀሳቀስ ዐቅማቸውን ያጎለብትላቸዋል” ብለዋል፡፡ ጀርመን ታንኮች ለመለገስ በመወሰኗም ባይደን አድንቀዋል፡፡