በእንግሊዝ የከለላ ጠያቂዎች ጉዳይ ውዝግብ ቀጥሏል

  • ቪኦኤ ዜና

በጀልባ ተጭነው ባህር ለማቋረጥ የሚሞክሩ የአፍሪካ ፍልሰተኞችን ያሳያል፡፡

በትናንሽ ጀልባዎች እንግሊዝ የገቡ ከለላ ጠያቂዎችን ወደ ርዋንዳ ለመላክ ለንደን ይዛው የነበረ ዕቅድ ‘ህገ-ወጥ ነው’ ተብሎ የተላለፈው ውሣኔ እንዲቀለበስ የሚጠይቅ አቤቱታ በመጭው ሣምንት አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ፊት እንደሚቀርብ ተገለፀ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ መንግሥት በአሥሮች ሺሆች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ ምሥራቅ አፍሪካዪቱ ርዋንዳ ለማዛወር የያዘውን ዕቅድ ‘ርዋንዳ ለስደተኞች መጠለያነት እንደ አስተማማኝ ሦስተኛ ሃገር ልትታይ አትችልም፤ ዕቅዱም ህጋዊ አይደለም” ሲል የለንደኑ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ባለፈው ሰኔ ውድቅ አድርጎት ነበር።

ይህ የችሎቱ ብይን የእንግሊዝ መንግሥት “ጀልባዎቹን ማስቆም” ሲል የሰየመውን ዕቅዱን ‘በብርቱ ያደባየ ነው’ ተብሏል።

ጉዳዩ የፊታችን ሰኞ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎት መታየት ሲጀምር ከሶሪያ፣ ከኢራቅ፣ ከኢራን፣ ከቪየትናምና ከሱዳን እንግሊዝ ለገቡት ፍልስተኞች የቆሙት ጠበቆችና የመንግሥቱ ነገረፈጆች የቀደመው ችሎት ውሣኔ እንዲፀና ወይም እንዲሠረዝ ለማስደረግ ሙግት እንደሚገጥሙ ይጠበቃል።

ኢሚግሬሽንን ቅድሚያ ከሚሰጧቸው አምስት ጉዳዮች አንዱ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚንስትር ሱናክ ውሳኔው በፈለጉት መንገድ ካልሄደ ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ተገምቷል።

ጉዳዩን በዕቅዳቸው መሠረት ካሳኩም በሚቀጥለው ዓመት ከሚካሄደው ምርጫ በፊት በተሰባሰቡት የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች በሃያ ነጥብ እየተመራ ላለው ወግ አጥባቂ ፓርቲያቸው የማንሠራራት ዕድል ያስገኝለት ይሆናል ተብሏል።