በኡጋንዳ የ70 ዓመቷ አዛውንት መንታ ወለዱ

ወላጇ ሳፊና ናሙክዋያ

በኡጋንዳ፣ የ70 ዓመቷ አዛውንት ትናንት መንታ ልጆችን መውለዳቸውን ዶክተራቸው አስታውቀዋል። በአፍሪካ ረጅም ዕድሜ ያላቸው ወላድ መሆናቸው ተነግሯል።

ወላጇ ሳፊና ናሙክዋያ “ተአምር” ብለው የገለጹት ውልደት፣ በመዲናዋ ካምፓላ በሚገኝ የሴቶች የሕክምና ሆስፒታል የተከናወነ ሲሆን፣ በሆስፒታሉ መጸነስ እንዲችሉ ሳይንሳዊ ርዳታ ሲያገኙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ለሴቶች ሕክምናና እንዲሁም መጸነስ እንዲችሉ ርዳታ የሚያደርገው ሆስፒታል መሥራች የሆኑት ዶ/ር ኢድዋርድ ታማል ሳሊ፣ እናቲቱም ሆኑ ወንድ እና ሴት ሆነው የተወለዱት ሕፃናት በሆስፒታሉ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

“በሰባ ዓመቴ፣ ማርገዝም ሆነ መውለድ ወይም ሕፃናትን መንከባከብ እንደማልችል በተነገረኝ ወቅት፣ መንታ ወልጄ ተአምር አየሁ” ብለዋል አራሷ።

“ደስታዬን የምገልጽበት ቃላት የለኝም” ሲሉ አክለዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ “እንዳትወልጂ የተረገምሽ ነሽ” የተባሉት እናት ከሶስት ዓመታት በፊትም ሴት ልጅ መውለዳቸው ታውቋል።

የመንታዎቹ አባት ሆስፒታል መጥቶ ባለመጎብኘቱ ሳፊና ብስጭታቸውን ገልጸዋል።

“መንታ ሲወለድ ኃላፊነትም ስለሚጨምር ወንዶች አይወዱ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።