ኡጋንዳዊቷ የማራቶን አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጊ ፍቅረኛዋ ሰውነቷ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት ካቃጠላት ከቀናት በኋላ ህይወቷ ማለፉን የሆስፒታል ባለሥልጣናት ዛሬ ሐሙስ አስታውቀዋል።
በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ በማራቶን አገሯን ወክላ የተወዳደረቸው የ33 አመቷ አትሌት ቼፕቴጊ ባለፈው እሁድ ኬንያ ውስጥ በደረሰባት ጥቃት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰውነቷ ክፍል ተቃጥሏል፡፡ ቼፕቴጊ እአአ ከ2021 ጥቅምት ወር ወዲህ ኬንያ ውስጥ የተገደለች ሦስተኛ ሴት አትሌት ሆናለች።
የኡጋንዳ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ሩካሬ በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "የኦሎምፒክ አትሌታችን ሬቤካ ቼፕቴጊ በፍቅረኛዋ በደረሰባት አስከፊ ጥቃት በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቷ ማለፉን ሰምተናል" ብለዋል።
“ነፍሷ በሰላም እንድታርፍ እንመኛለን፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን። ይህ ታላቋን አትሌታችንን እንድናጣ ያደረገ ትርጉም የለሽ የፈሪ ተግባር ነው" በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በፓሪሱ ውድድር 44ኛ ሆና ያጠናቀቀችው ቼፕቴጊ ጥቃቱ ከደረሰባት በኋላ በኬንያ ኤልዶርት ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላት ቆይታ ዛሬ ጠዋት ህይወቷ አልፏል። አሟሟቷን "አሳዛኝ" ሲሉ የገለጹት የኡጋንዳ ስፖርት ሚኒስትር ፒተር ኦግዋንግ በበኩላቸው የኬንያ ባለስልጣናት የሞተችበትን ሁኔታ በማጣራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ቼፕቴጊ ትኖርበት እና ትሰለጥንበት በነበረው ኬንያ ውስጥ መገደሏ በኬንያ ሴት ስፖርተኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የበለጠ አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።