ዩጋንዳ የመጀመሪያዎቹን የአፍጋን ስደተኞች ተቀበለች

  • ቪኦኤ ዜና

የአፍጋኒስታን ስደተኞች ዩንጋንዳ ኢንተቤ ወደ ተዘጋጀላቸው ጊዚያዊ ማረፊያ ተወስደዋል

ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተረከበ በኋላ፣ አገር ጥለው የተሰደዱ ስደተኞችን የጫነው አውሮፕላን፣ ዛሬ ረቡዕ ማለዳው ላይ፣ ዩንጋንዳ ኢንተቤ ከተማ ውስጥ ማረፉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

የዩንጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ሴቶች ህጻናትና ወንዶች የሚገኙበት 51 የአፍጋኒስታን ዜጎች ወደ ተዘጋጀላቸው ጊዚያዊ ማረፊያ ተወስደዋል፡፡

ኡጋንዳ የአፍጋኒስታን ስደተኞችን የተቀበለችው፣ ስደተኞችን ለመቀበል፣ ችግር ላይ የወደቁትን በመርዳት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳሳቢ በሆነው ጉዳይ ተሳታፊ ለመሆን፣ በምትከተለው ፖሊሲዋ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ እንደሚያስረዳው ኡጋንዳ ወደ 2ሺ የሚሆኑ የአፍጋን ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ መስማማቷን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ኡጋንዳ በዓለም ላይ በርካታ ስደተኞችን ከተቀበሉ ጥቂት አገሮች መካከል ስትሆን ወደ 1.5 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ናት፡፡