ሙሴቪኒን ሰድቧል የተባለው ወጣት በፍ/ቤት ጥፋተኛ ተባለ

ቲክቶክ

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በሕዝብ ፊት ይገረፉ የሚል መልዕክት በቲክቶክ ያስተላለፈው የ21 ዓመት ወጣት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል።

ኢማኑዌል ናቡጎዲ፤ ሙሴቪኒ በፍ/ቤት ሲዳኙ የሚያሳይ ሐሰተኛ ቪዲዮ አቀናብሮ አጋርቷል በሚልና፣ “ፕሬዝደንቱን በመስደብና በጥላቻ ንግግር” ክስ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ኢማኑዌል በሰባት ዓመት እሥራት እንዲቀጣ ጠይቋል።

ኢማኑዌል ባለፉት ሁለት ቀናት ፕሬዝደንቱንና ቤተሰባቸውን ተሳድበዋል በሚል በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በፍ/ቤት ከተወሰነባቸው አራት ግለሰቦች አንዱ ነው።

ሃገሪቱን ለ38 ዓመታት የመሩትን ሙሴቪኒ በቲክቶክ ሰድቧል የተባለ ሌላ የ21 ዓመት ወጣት ባለፈው ሐምሌ በስድስት ዓመት እሥር ተቀጥቷል።

ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኘው ሌላው ደራሲ ካክዌንዛ ሙሴቪኒን እና ልጃቸውን ተሳድቧል በሚል ከሦስት ዓመታት በፊት በቁጥጥር ውሎ ነበር። በስደት ጀርመን የሚገኘው ካክዌንዛ በአንድ ወር እስር ቆይታው ወቅት ስቃይ እንደደረሰበት ተናግሯል።