በምሥራቃዊ ዩጋንዳ በተከሰተ የመሬት ናዳ ቢያንስ 30 የሚሆኑ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ባለሥልጣናቱ አክለውም የሟቾቹ ቁጥር ከተጠቀሰውም ሊበልጥ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ላለፉት ጥቂት ቀናት በሀገሪቱ ከባድ ዝናብ ሲጥል የነበረ ሲሆን፣ ጎርፍ እና የመሬት ናዳ መከሰታቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ መንግሥት ብሔራዊ የአደጋ ማስጠንቀቂያ አውጇል።
ከመዲናዋ ካምፓላ የአምስት ሰዓት ርቀት ላይ የምትገኘው ማሱጉ መንደር ትላንት ረቡዕ የመሬት ናዳው ከተከሰተባቸው መንደሮች አንዷ ስትሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች የአደጋውን አስከፊነት አሳይተዋል።
የወርዳው ኮሚሽነር 30 ሰዎች ኅይወታቸው እንዳለፈ አስታውቀዋል። እስከአሁን የአንድ ሕፃንን ጨምሮ ስድስት አስከሬኖች መገኘታቸውንም ተናግረዋል።
የአደጋውን ከባድነትና የሸፈነውን ስፋት በመመልከት በርካታ ሰዎች የደረሱበት እንደማይታወቅና ምናልባትም ናዳው ሥር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የዩጋንዳው ቀይ መስቀል ቃል አቀባይ በበኩሉ 13 አስከሬኖችን ማግኘታቸውንና አደጋውም በበርካታ መንደሮች መከሰቱን አስታውቀዋል።