በዩጋንዳ ለበርካታ ዓመታት ስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን በመቃወም፤ ቀዳሚ የሆነው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቦቢ ዋይን ዛሬ ማክሰኞ ዋና ከተማዋ ካምፓላ ሰሜናዊ ዳርቻ በደህንነት አባላት በተተኮሰ ጥይት እግሩን መመታቱን ፓርቲው አስታውቋል።
ከፖፕ ሙዚቃ ወደ ፖለቲካ ፊቱን ያዞረው እና በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን የተባለው ሮበርት ኪያጉላኒ በጎርጎርሳዊያኑ 2021 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዩጋንዳን ለአራት አስርት ዓመታት ያህል የመሩትን ሙሴቬኒን በመከተል በ2ኛነት አጠናቋል።
"የደህንነት ሰራተኞች በፓርቲው ፕሬዚዳንት ላይ የግድያ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ቦቢ ዋይን እግሩ ላይ በጥይት ተመትቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል" ሲል የብሔራዊ አንድነት ፓርቲ በኤክስ ገጹ ላይ አመልክቷል ፡፡
ፓርቲው ይኸን ይበል እንጂ ኤን ቲቪ የተባለ የሀገር ውስጥ ገለልተኛ የስቴሌቭዢን ጣቢያ ቦቢ ዋይን ፖሊስ ደጋፊዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ በመተኮሱ በተፈጠረ ግጭት መጎዳቱን ዘግቧል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ኦኒያንጎ አስተያየት እንዲሰጡ በሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም፡፡