የዩጋንዳውን ፕሬዚዳንት ዮዌሪ መሴቬኒን "ፌስ ቡክ ላይ ሰድበዋል" በሚል ባለፈው ወር ታስረው የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶክተር ስቴላ ኛንዚ ዛሬ በዋስ ተለቅቀዋል፡፡
ዶክተር ኛንዚ ዛሬ ወደ ችሎት ሲገቡ እጅግ የተጎሣቆለ ገፅታ ይታይባቸው እንደነበረ ተዘግቧል፡፡
ወትሮ ንቁ፣ ተገዳዳሪና ተናጋሪ የነበሩት ኛንዚ በሦስት ሴት የወኅኒ ዘቦች ተደጋግፈው ነበር ዳኛ ፊት የቀረቡት፡፡ ዳኛው ጄምስ ኢሬሚዬ ውሣኔአቸውን ከማሰማታቸው በፊት እረፍት እንደተወጣ ኛንዚ ተዝለፍልፈው ወድቀዋል፡፡
ለማንኛውም ሰዉም ከእረፍት ተጠራ፤ ዳኛውም ውሣኔአቸውን አሰሙ፡፡
"በተሰጠኝ ሥልጣን መሠረት ተጠርጣሪዋ በአሥር ሚሊዮን ሽልንግ ዋስ እንዲፈቱ ወስኛለሁ፡፡" አሉ ዳኛው፡፡
ኛንዚ ለዛሬው የዋስ መብት መጠበቅ ከመድረሳቸው በፊት ለአራት ሣምንታት እሥር ላይ ቆይተዋል፡፡
«ኢንተርኔትን ያለአግባብ በመጠቀም» እና «ጎጂ ንግግሮችን በኢንተርኔት ማውጣት» የሚል ነበር የተሰማባቸው ክሥ፡፡ ኛንዚ መሴቪኒን «መንታ ቂጥ» ሲሉ ፌስቡክ ላይ ፅፈውባቸዋል ተብሏል፡፡ /ችሎት ፊት የቀረበ የክሥ ጭብጥ በመሆኑ ነው ቃሉን በግልፅ ለመጥራት የተገደድነው፤ በእኛ በኩል ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡/
ይህ ኢንተርኔት ላይ የወጣ ፅሁፍ ፕሬዚዳንቱ ገቢያቸው አነስተኛ የሆነ ቤተሰቦች አባላት ለሆኑ ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን በነፃ ለማዳረስ ቀደም ሲል ገብተውት የነበረውን ቃል እንዲጠብቁ ለማስገደድ ስቴላ ኛንዚ የከፈቱት ዘመቻ አካል ነው፡፡
በችሎቱ ፊት ስለ ኛንዚ የተሟገቱት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ጠበቃው ኒኮላስ ኦፓዮ ደንበኛቸው የደም ግፊትና የወባ ችግሮች እንዳሉባቸው ገልፀዋል፡፡
"ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ቢሆን ስቴላን በዋስ በመልቀቁ ደስ ብሎናል፤ ባለሥልጣናቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሰው ዶክተር ኛንዚን እንደገና እንዳያስሩና እንዳያውሉም እንፀልያለን፡፡ አሁን ነፃ በመሆናቸው ለችሎት ስለሚሰጡት መልስም በተገቢው ሁኔታ መወያየት እንችላለን» ብለዋል ጠበቃቸው፡፡
ዳኛው ውሣኔአቸውን ከማሰማታቸው በፊት የተናገሩት የመንግሥቱ አቃቤ ሕግ ጆናታን ሙዋጋኛ ለተከሣሿ የዋስትና መብት ቢጠበቅላቸው እንደማይቃወሙ ገልፀዋል፡፡ "አሁን ተከሣሿ እንደታመመች ተነግሮናል፡፡ ክቡርነትዎ ይህቺ በዋስ የተለቀቀች ተከሣሽ ካሁን በኋላ በኢንተርኔት የሰደበችውንም ሰው ሆነ የቤተሰቡን አባላት እንደገና እንዳትሰድብ እንዲያሳስብልኝ እጠይቃለሁ» ብለዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ተሟጋች ቡድን በኛንዚ ላይ የተመሠረተውን ክሥ «አስገራሚና ሃሣብን በመግለፅ ነፃነት ላይ የተጣለ ስድብ» ነው ብሎታል፡፡ ክሡ ሙሉ በሙሉ እንዲሠረዝም ጠይቋል አምነስቲ፡፡
የኛንዚ ጉዳይ ለፊታችን ግንቦት 17 ተቀጥሯል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5