ሙሴቪኒ ልጃቸው የጦር ኃይሉን እንዲመሩ ሾሙ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩጋንዳው የረጅም ዘመን ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ ጄነራል ሙሁዚ ኬንሩጋባ

የዩጋንዳው የረጅም ዘመን ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጃቸው የአገሪቱን መከላከያ ኃይል እንዲመሩ ሾመዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ዲፕሎማሲያዊ ቁጣን ያስከተሉ መልዕክቶችን በማስተላለፋቸው የሚታወቁት ሙሁዚ ኬንሩጋባ፣ ለቦታው ብቁ እንዲሆኑ አባታቸው ሲያዘጋጇቸው እንደነበር የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

አባታቸውን ለመተካት ይፈልጋሉ የሚለውን ወሬ የሚያስተባብሉት የ49 ዓመቱ ጀኔራል ሙሁዚ ኬንሩጋባ፣ በዩጋንዳ መከላከያ ኃይል ውስጥ በፍጥነት ዕድገት ሲያገኙ ቆይተዋል።

ኬንሩጋባ፣ በመጪው 2026 በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባለፈው ዓመት ካስታወቁ በኋላ መልሰው መልዕክቱን አጥፍተዋል።

ከሁለት ዓመታታ በፊት ኬንያን ለመውረር በማኅበራዊ ሚዲያ መዛታቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱን ጉዳይ በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት እንዳያስተላልፉ አባታቸው ሙሴቪኒ ነግረዋቸዋል።

ሙሴቪኒ ለኬንያ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ልጃቸውን ግን “በጣም ጥሩ የጦር ጀኔራል” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ኬንሩጋባ ለአባታቸውም አልተመለሱም። “እስከ መቼ በሽማግሌዎች እንመራለን። ሕይወታችንን አበላሹ፡፡ አይበቃም ወይ” ሲሉ በአንድ ወቅት መልዕክት አስተላልፈዋል።