በተመድ የአሜሪካ ልዑክ ቻድ ውስጥ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችን ጎበኙ

ፎቶ ፋይል፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ልዑክ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ

በቻድ ድንበር ከተማ በሱዳን ጦርነት የተፈናቀሉ የሀገሪቱ ዜጎችን ያነጋገሩት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ልዑክ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ምክትል መሪ እና የዋና አዛዡ ሞሃመድ አምዳን ዳግሎ ወንድም የሆኑት አብደልራሂም አምዳን ዳግሎን ጨምሮ፣ በከፍተኛ ባለሥልጣኖች እና አዛዦች ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል አስታውቀዋል።

የጎሳ እና የጾታ ጥቃትን ሸሽተው ቻድ ውስጥ የሚገኙ ሱዳናውያንን ያነጋገሩት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ በሱዳን ግጭት ውስጥ የጅምላ የጭካኔ ጥቃት እንዳይኖር አሜሪካ የሚቻለውን ሁሉ ታደርጋለች ብለዋል። በሱዳን ሕዝብ ላይ በደረሱት አንዳንድ የጭካኔ ተግባራት መደንገጣቸውንም አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ በአብደልራሂም ሃምዳን ዳግሎ የተያዙና አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች እና ተየያዥ ይዞታዎችን በሙሉ ያገደ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

አብደልራሂም ሃምዳን ዳግሎ ማዕቀቡ ኢፍትሃዊ ነው ሲሉ ትናንት በቪዲዮ በለቀቁት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።