የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አሕመት ዳቩቶግሉ ሀገራቸው ባለፈው ሳምንት በቱርክና በሶርያ ድንበር ላይ የሩስያን ተዋጊ አይሮፕላን ተኩሳ በመጣልዋ ይቀርታ አትጠይቅም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኔቶ ማለት ከሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ሀገሮች ድርጅት ሀላፊ ጀንስ ስቶልትበርግ (Jens Stoltenberg) ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጣኞች በሰጡት መግለጫ የቱርክ ሃይሎች የሀገሪቱን የአየር ግዛት የመጠበቅ ግዴታቸውን ነው የፈጸሙት ሲሉ ተናግረዋል። ዳቩቶግሉ አያይዘውም የሩስያው ፕረዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ለተዋጊ አይሮፕላኑ መመታት ምላሽ በቱርክ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመጣል የወሰዱትን ውሳኔ እንደሚቀለብሱ ተስፋ አድርጋለሁ ብለዋል።
በቱርክ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ሩስያ ከቱርክ የምታሰገባቸውን ምርቶች ይገድባል፣ በሩስያ የሚሰሩት ቱርካውያን ኩንትራት እንዳይራዘም ያግዳል። በሩስያ የሚሰሩት የቱርክ ኩባንያዎችንም ይመለከታል።
የቱርክ ፍራፍሬና አትክልት ወደ ሩስያ እንዳይገባ የሚያግደው ማዕቀብ በቀጣዮቹ ሳምንታት ገቢራዊ እንደሚሆን የሩስያ መንግስት ዛሬ አስታውቋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ፕረዚዳንት ፑቲን ፓሪስ በሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ ጎን ከቱርኩ ፕረዚዳንት ረሰፕ ታይብ ኤርዶጋን (Recep Tayyip Erdogan) ጋር ተገናኛተው እንደማይነጋገሩ የክርምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮፍ ገልጸዋል።
ቱርክ አይሮፕላኑ የግዛቴን የአየር ድንበር በመጣሱ ነው ተኩሸ የጣልኩት ትላለች። ሩስያ ግን ተዋጊው አይሮፕላንዋ ከሶርያ ግዛት አልወጣም ብላለች። የአንድ የሩስይ ፓይለት አስከሬን ዛሬ ከአንካራ ወደ ሩስያ አምርቷል። የሩስያና የሶርያ ሃይሎች ነበሩ ሁለተኛውን ፓይለት ከሞት ያዳኑት። አንድ ሌላ ሩስያዊ ወታደር ደግሞ በማዳኑ ጥረት ወቅት ተገድሏል። የዜና ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5