ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ተስማሙ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ፣

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ፣ ከሶማሊያ ተለይታ የራስ-ገዝ አስተዳደር ከመሰረተችው ሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ጋራ በተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት ምክኒያት ለአንድ ዓመት ገብተውበት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ለማቆም ዛሬ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር አንካራ ላይ ያደረጉትን ሦስተኛ ዙር፣ ድርድር ተከትሎ የሶማሊያ መሪ ሀሰን ሼክ መሀሙድ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአንዳቸው የሌላውን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተስማምተዋል።

ኤርዶዋን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድን እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት ዛሬ ለየብቻ ተቀብለው ካነጋገሯቸው በኋላ ነው ስምምነቱ ይፋ የተደረገው።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ የዛሬ ስብሰባው “ጠቃሚ” እና በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ለሚደረግ ውይይት መንደርደሪያ እንደሚኾን አስታውቆ ነበር። መሀሙድ አንካራ የገቡት ትላንት ማክሰኞ ሲኾን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደግሞ ዛሬ ረቡዕ አንካራ መግባታቸውንና ከኤርዶዋን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኤክስ ላይ ባወጣው ጽሑፍ አስታውቆ ነበር።

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ እና የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን "ታሪካዊ" የመግባቢያ ስምምነት ከፈረሙበት እነደ አውሮፓውያን ከጥር 1 ቀን 2024 ጀምሮ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።

የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ዲፕሎማሲያዊ እውቅና በአጸፋው ለማግኘት ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የባሕር በር ለ50 ዓመታት በኪራይ እንደሚሰጥ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት ሥምምነቱን በጽኑ በመቃወም ውድቅ አድርጎ አምባሳደሩንም ጠርቶ እንደነበር ይታወሳል።

ሶማሊያ ስምምነቱን “ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል” ያለችው ሲሆን “በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ ግልጽ የሆነ ጥሰት ፈጽማለች" ብላ ኢትዮጵያን ስትከስ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ ለመግባቢያ ስምምነቱ ተገቢነት ብትሟገትም ለሶማሌላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ በይፋ አረጋግጣ ግን አታውቅም።

ባለፈው ሐምሌ እና ነሀሴ ወራት በቱርክ የተካሄዱ ሁለት ዙር ንግግሮች በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ባይችሉም፣ በሦስተኛው ዙር ግን ውይይት ግን ሁለቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን ለመፍታት ተስማምተዋል።