በቱኒዚያ ያሉ አፍሪካዊ ስደተኞች ወደ ሌላ አገር እንዲዛወሩ ጠየቁ

በአገሪቱ ወከባና እንግልት ይደርስብናል በሚል ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች በቱኒዚያ መዲና ቱኒዝ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት በመሰባሰብ ወደ ሌላ አገር እንዲዛወሩ ጠይቀዋል፡፡

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ካይስ ሳይድ ስደተኞችን ከነቀፉና፣ “የቱዚያውያንን ማንንነት ሊያጠፉ የመጡ ናቸው” ብለው ከተናገሩ በኋላ፣ ጥቃትና እንግልት እንደደረሰባቸው በአብዛኛው ከሱዳን የመጡትና በመንግሥታቱ ድርጅት ጽ/ቤት የተሰባሰቡት ስደተኞች ተናግረዋ፡፡

በቱኒዚያ ከጥቃት የሚጠብቃቸው እንደሌለና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአውሮፓ ሕብረት በሌላ ደህንነታቸው መጠበቅ የሚችልበት አገር መሥፈር እንዲችሉ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ስደተኞቹ ላለፉት 10 ቀናት በመንግሥታቱ ድርጅት ጽ/ቤት ተቃውሞ ሲያሰሙ ሰንብተዋል፡፡

ምዕራባውያንና አፍሪካውያን የቱኒዚያ ሸሪኮች ወቀሳ ካቀረቡ በኋላ፣ የቱኒዚያ መንግሥት ስደተኞቹ ጥቃት ሲገጥማቸው የሚያሳውቁበትን የስልክ መስመር እንዲሁም የጤናና የስነ ልቦና ድጋፍ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል ተብሏል፡፡