የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የገንዘብ ኃላፊ የነበሩት አለን ዋይስልበርግ በሃሰት በመመስከር የአምስት ወራት እሥር ተፈርዶባቸዋል።
የኒው ዮርክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ ባቀረቡት ክስ፣ ዋይስልበርግ ለፍርድቤት የምስክርነት ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት ዋሽተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው፣ ጥፋተኛ መሆናቸውን ባለፈው ወር አምነው ነበር።
ዋይስልበርግ ጥፋተኛ የተባሉት በማንሃተን የሚገኘው የዶናልድ ትረምፕ ቅንጡ መኖሪያ ቤት ‘ፔንትሃውስ’ ዋጋው በሒሳብ መዝገብ ውስጥ ተጋኖ ቀርቧል የሚለውን ክስ በተመለከተ በሰጡት ምስክርነት ዋሽተዋል በሚል ነው።
ዛሬ በዋለው ችሎት የአምስት ወራት እሥር የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ወዲያውኑ የእጅ ካቴና ተጠልቆላቸዋል።
የ76 ዓመቱ ዋይስልበርግ የእሥር ቅጣት ሲደርስባቸው ለሁለተኛ ግዜ ነው። ባለፈው ዓመት ከኩባንያቸው ባገኙት 1.7 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ላይ ግብር አልከፈሉም በሚል የ100 ቀናት እሥር ተፈርዶባቸው ነበር።