ትረምፕ ሜክሲኮ ከጓቴማላ እየገቡ ያሉ ፍልሰተኞችን እንድታስቆም አስጠነቀቁ

  • ቪኦኤ ዜና
ሜክሲኮ ከጓቴማላ እየገቡ ያሉ ግዙፍ ቁጥር ያላቸውን ፍልሰተኞች ካላስቆመች ከሜክሲኮ ጋር ባላት ድንበር ላይ ጦር እንደሚያቆሙ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ አስጠነቀቁ።

ሜክሲኮ ከጓቴማላ እየገቡ ያሉ ግዙፍ ቁጥር ያላቸውን ፍልሰተኞች ካላስቆመች ከሜክሲኮ ጋር ባላት ድንበር ላይ ጦር እንደሚያቆሙ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ አስጠነቀቁ። ባለፈው ሣምንት ከሆንዱራስ የተነሡ ሦስት ሺህ የሚሆኑ ፍልሰተኞች ጓቴማላንና ሜክሲኮን አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት እየተጓዙ መሆናቸው ተዘግቧል።

በእነዚያ ፍልሰተኞች መካከል “ወንጀለኞች አሉ” ያሉት ፕሬዚዳንት ትረምፕ ሜክሲኮ እንቅስቃሴዎቸውን እንድትገታ በጥብቅ እንደሚያስጠነቅቁ አስታውቀዋል። ዩናይትድ ስቴትስ “በደቡብ ድንበሯ ላይ የሚጣሉ ጥቃቶች ከካናዳና ከሜክሲኮ ጋር የገባችባቸውን የንግድ ውሎች ይጎዳሉ” ሲሉም አሳስበዋል ፕሬዚዳንት ትረምፕ።

ለዚህ ፕሬዚዳንት ትረምፕ በትዊተር ላወጡት ማስጠንቀቂያ ከአንድ የሃገራቸው ራዲዮ ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ምላሽ የሰጡት የሜክሲኮ አዲስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሴሎ ኤብራይድ “ፕሬዚዳንቱ የፖለቲካ ስሌት እየሠሩ ነው” ሲሉ ጉዳዩን የመጭው የሃገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤትና የአካባቢ ሥልጣናት ምርጫ ጋር አያይዘውታል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ከተሰናባቹ የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ኤንሪኬ ፔኛ ኚዬቶ ጋር ለመወያየት ዛሬ ሜክሲኮ ሲቲ ገብተዋል።