ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ፖለቲከኛ እና የቀድሞ ጋዜጠኛ የነበሩትን ኬሪ ሌክ በመንግሥት ለሚደገፈውና ዓለም አቀፍ ስርጭት ላለው የአሜሪካ ድምጽ ዲሬክተርነት እንዲሾሙ ማጨታቸውን ትላንት ረቡዕ አስታውቀዋል።
ትረምፕ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተሰኘው ማኅበራዊ መድረካቸው ላይ እንዳስታወቁት፣ ኬሪ ሌክ የቪኦኤ ዲሬክተር ኾነው እንደሚሾሙ አስታውቀዋል። ኬሪ ሌክ የትረምፕ የቅርብ የፖለቲካ አጋርና አሪዞና በሚገኘው የፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ደግሞ የቀድሞ ዜና አቅራቢ ነበሩ።
ሌክ ለ27 ዓመታት በጋዜጠኝነት የሠሩ ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2021 ዓ.ም ለአሪዞና አገረ ገዢነት ለመወዳደር ሲሉ ሥራቸውን አቁመዋል።
በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ለአሜሪካ ሴኔት ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ሌክ፣ በምርጫ ዘመቻዎቻቸው አሪዞና “የአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲዎች ተምሳሌት” መሆን አለባት ብለዋል።
‘ዩ ኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ’ (USAGM) በመባል ለሚታወቀውና ለአሜሪካ ድምጽ እና ለሌሎችም በመንግሥት ለሚደገፉ የሥርጭት ጣቢያዎች እናት ድርጅት ለኾነው መንግሥታዊ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ እንደሚሾሙ ትረምፕ ትላንት ረቡዕ ጨምረው አስታውቀዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው በፕሬዝደንቱ የሚታጭ ሲኾን፣ በሕግ አውጪው ሸንጎ ወይም ሴኔት መጽደቅ ይኖርበታል። ለዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመርጡት ግለሰብ ኬሪ ሌክን እንደሚሾሙና ሁለቱ ሹሞች በቅርበት እንደሚሠሩም ትረምፕ ጨምረው አስታውቀዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ‘ዩ ኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ’ (USAGM) በተቀመጠለት ተልዕኮ መሠረት ነጻ ብዙሃን መገናኛዎች ውስን ወደሆኑባቸው ሃገራት ተአማኒና ትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥራዎች መሰራጨታቸውን ያረጋግጣል።
የቪኦኤ የወቅቱ ዲሬክተር ማይክ አብራሞዊትዝ ዛሬ ሐሙስ ማለዳ ለድርጅቱ ሠራተኞች በላኩት የኢሜይል መልዕክት፣ ኬሪ ሌክን በተመለከተ የወጣውን መረጃ ረቡዕ ምሽት መመልከታቸውንና፣ በማኅበራዊ መድረክ ላይ ከወጣው ውጪ ሌላ ተጨማሪ መረጃ እንዳልተሰጣቸው አስታውቀዋል።
“በዩ ኤስ ጂ ኤምም ሆነ በቪኦኤ የሚደረጉ የሥልጣን ሽግግሮችን በመልካም እቀበላለሁ” ያሉት አብራሞዊትዝ፣ የቪኦኤን ዲሬክተር ሹመት በተመለከተ “ከአዲሱ አስተዳደር ጋራ ለመተባበርና የሽግግር ሂደቱንም ለመከተል እሻለሁ” ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር 2020 ዓ.ም የኤጀንሲውን አስተዳደር እንደገና ስለማዋቀር የወጣው ሕግ
የዩ ኤስ ጂ ኤም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሥሩ ያሉ ኃላፊዎችን የመቅጠርና የማባረር ሥልጣን ተሰጥቶታል። ነገር ግን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 2020 ዓ.ም. ላይ በሁለቱም ፓርቲዎች በጋራ በወጣው ሕግ መሠረት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወይም አስፈጻሚዋ ኃላፊዎቹን ለመቀየር የ’ዓለም አቀፍ ሥርጭት አማካሪ ቦርድ’ የተባለው አካል በድምጽ ብልጫ መወሰን አለበት፡፡
ቦርዱ የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ እና በፕሬዝደንቱ የሚሾሙ ስድስት ዓባላት ሲኖሩት፣ እያንዳንዱ ዓባልም የተለያየ የአገልግሎት ዘመን አለው። የቦርዱ ኃላፊነትም የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥርጭት ጣቢያዎቹን የኤዲቶሪያል ነጻነትና ሃቀኛ የሆነ መርህን እንዲያከብሩና እንዲያረጋግጡ እንዲሁም ጋዜጠኝነት የሚጠይቀው ከፍተኛ መመዘናዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ነው።
ኬሪ ሌክ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለቪኦኤ ኃላፊነት በመታጨታቸው ክብር እንደሚሰማቸው አስታውቀዋል። ቪኦኤ “እጅግ አስፈላጊ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም ነው” ያሉት ሌክ “ዲሞክራሲንና እውነትን” የሚያበረታታ ተቋምም ነው ሲሉ አክለዋል።
“በእኔ አመራር ቪኦኤ በተልዕኮው የላቀ አፈጻጸም ይኖረዋል። የአሜሪካንን ስኬትም ለዓለም ያሳውቃል” ብለዋል ሌክ።
ቪኦኤ የኬሪ ሌክን አስተያየት ለማግኘት በዘመቻ ድህረ ገጻቸው ላይ በሚገኘው የሚዲያ ክፍል አማካይነት ሞክሯል። ይህ ዜና እስከታተመበት ሰዓት ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ቪኦኤ በሳምንት 354 ሚሊዮን ለሚሆኑ አድማጮቹ በ49 ቋንቋዎች የሚያሰራጭ ሲሆን፣ የወቅቱ ዲሬክተር የሆኑት ማይክ አብራሞዊትዝ የፍሪደም ሃውስ የቀድሞ ፕሬዝደንትና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ለ 24 ዓመታት አዘጋጅ ነበሩ።