የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጄ. ትረምፕ የበኩር ልጅ ዶናልድ ትረምፕ (ትንሹ) የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣን ናቸው ብሎ አምኖባቸው ከነበረ አንዲት ግለሰብ ጋር የሂላሪ ክሊንተንን የፕሬዚዳንትነት ፉክክር ሊጎዳ ይችላል ተብሎ የታሰበ መረጃ ስለማግኘት ለመነጋገር ተገናኝቶ እንደነበረ የወጡ መረጃዎችን የሚያጠናክሩ የኢሜል ልውውጦችን ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ኢሜሎች ትረምፕ እንዲሁም በምርጫ ሂደቱ ወቅት የዘመቻ ቡድናቸው ከሩሲያ መንግሥት ጋር ተመሣጥሯል በሚል የገቡበትንና እስካሁንም መውጫና መቋጫ ያልተገኘለትን ችግር ይበልጥ ያባባሰው መሆኑ እየተሰማ መሆኑን የዋይት ሃውስ ሪፖርተራችን ፒተር ሃይንላይን ዘግቧል፡፡
በትንሹ ዶናልድ ትረምፕ ትናንት [ማክሰኞ] ይፋ የተደረጉት ኢሜሎች የሚናገሩት የሩሲያ መንግሥት አቃቤ ሕግ ናቸው የተባሉ ግለሰብ “ሩሲያና መንግሥቷ ለሚስተር ትረምፕ ያላቸው ድጋፍ አካል የሆነ እጅግ አንገብጋቢና በከፍተኛ ደረጃ የተያዘ መረጃ” ሊያካፍሏቸው ያቀረቡላቸውን ጥሪ በደስታ መቀበላቸውን ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ትረምፕ ስለጉዳዩ የሰጡትን እጥር ያለች “ልጄ ከፍ ያለ ምግባር ያለው ሰው ነው፤ ግልፅነቱንም አደንቃለሁ፡፡ ከዚያ በተረፈ ሁሉንም ነገር የምተወው ለራሱ ነገረ ፈጅና ከነገረ ፈጁም ውጭ ላሉ ነው፤ ከዚያ ውጭ የምጨምረው አንዳች ነገር አይኖረኝም” ሲሉ የሰጧትን ባለ አንድ መስመር መግለጫ የዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት ምክትል ቃል-አቀባይ ሴራ ኸካቢ ሳንደርስ ለጋዜጠኞች በንባብ አሰምተዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
በእነዚህ ትናንት ይፋ በተደረጉ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚዎቹ ዴሞክራቶች ፈጣንና ቆፍጠን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኢሜሎቹ ዋይት ሃውስ ክሊንተንን ለማሸነፍ የዘመቻ አከናዋኞቹ ከሩሲያ ጋር መመሣጠርና ሴራ የነበራቸው ስለመሆኑ እስካሁን ይዞት የቆየውን ክህደት ዋጋ ቢስ አድርገዋቸዋል ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሕዳጣኑ ዴሞክራቲክ እንደራሴዎች መሪ ቸክ ሹመር መግለጫ ሲሰጡ “ኢሜሎቹ መመሣጠርና መስተጋብር የነበረ ስለመሆኑ በአስተዳደሩና በፕሬዚዳንቱ ዘንድ ተይዞ ለቆየው የመግፋት ሃሣብ ፍፃሜ አበጅተውለታል” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩልም ቢሆን ሪፐብሊካኑም እንደራሴዎች ያመኑት አንድ ሃቅ አለ - 'እነዚህ ኢሜሎች የሚጥሉት ጠባሳ መልካም ገፅታን የሚያኖር አይደለም፡፡'በርግጥ እኒያ አቃቤ ሕግ የተባሉ ሴት 'የክሬምሊን ወኪል' የመባላቸውን ነገር ቢክዱም፤ 'በእጃቸው ነበር' የተባለው መረጃ ‘ይህንን ያህል ለጉዳት የሚሰጥ አልነበረም’ ቢባልም፡፡
የሴኔቱ አብላጫ እንደራሴዎች መሪ የሆኑት ሪፐብሊካኑ ሚች ማክኮኔል አሁን እየተካሄዱ ላሉት የምርመራ ሥራዎች ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡
"መላውን ምርመራ እያካሄደ ባለው የስለላና መረጃ ጉዳዮች ኮሚቴው ላይ ብዙ እምነት አለኝ፡፡ ሴናተር በር እና ሴናተር ዋረን ጉዳዩን በአግባቡ ይዘውታል፤ የሚደርሱበትን ይነግሩናል" ብለዋል፡፡
የዶናልድ ትረምፕ (ልጅየው) ኢሜሎች ቀደም ሲል ተነስተው የማያውቁ የሕግ ጥያቄዎችን እያስነሱ ነው፡፡ የምርጫ ሕግ ባለሙያ የሆኑት በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የበፋሎ የሕግ ትምህርት ቤት ባልደረባው ጄምስ ጋርድነር ከቪኦኤ ጋር በስካይፕ በተነጋገሩ ጊዜ “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከዚህ ቀደም ተነስቶ እንደማያውቅና ምንም እንኳ የተፃፉ ድንጋጌዎች ቢኖሩንም እጅግ በጣም ያልተለመዱ በሆኑ በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ላይ ተፈፃሚ እንዲደረጉ የተጠየቀበት ጊዜ እንዳልነበረ አመልክተዋል፡፡
ትረምፕ [ልጅየው] የሚናገሩት እንዳችም ጥፋት እንዳልፈፀሙ ነው፡፡ ከሩሲያዊቱ አቃቤ ሕግ ጋር በተገናኙ ወቅትም “አንዳችም የሚረባ መረጃ አላገኘሁም” ብለዋል፡፡
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5