ትረምፕ ጥፋተኛ በተባሉበት ክስ ዳኛው የቅጣት ውሳኔ እንዳይሰጡ እንዲታገድላቸው ጠየቁ

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ጥፋተኛ በተባሉበት የአፍ ማሳዢያ ክፍያ ክስ ጉዳይ ዳኛው የቅጣት ውሳኔያቸውን እንዳያሰሙ እንዲታገድ ጠበቆቻቸው ጠቅላይ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል።

ዳኛዋን መርቻን ፣ ትረምፕ ባለፈው ሐምሌ የንግድ ሰነዶችን በማጭበርበር በ34 ክሶች ጥፋተኛ ኾነው በመገኘታቸው የቅጣት ውሳኔያቸውን ከነገ በስቲያ ዐርብ ሊሰጡ ቀጠሮ ይዘዋል።

የቅጣት ውሳኔው መሰማቱ በፕሬዝደንታዊ ተቋሙና በፌዴራል መንግሥቱ ሥራ ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ተጽዕኖ እና ጉዳት ያደርሳል በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲያግድ የትረምፕ ጠበቆች ጠይቀዋል።

ዳኛው በትረምፕ ላይ የእሥርም ኾነ የገንዘብ ቅጣት ወይም ወይም የአመክሮ ገደብ ያለው ትዕዛዝ እንደማያስተላልፉባቸው አመላክተዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛው እስከ ነገ ሐሙስ ድረስ መልስ እንዲሰጡ ጠይቋል።

የትረምፕ ጠበቆች ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ከዚህ በፊት ሰጥቷቸው የነበረውን ያለመከሰስ መብት በመጥቀስ ዐርብ ሊሰማ ቀጠሮ የተያዘለትን የቅጣት ውሳኔ እንዳይከናወን ጠይቀዋል።

የትረምፕ ጠበቆች በተጨማሪም ከክሱ ጋራ ተያይዘው የቀረቡ አንዳንዶቹ ማስረጃዎች በፕሬዝደንታዊ ያለመከሰስ መብት መሠረት ይፋ መውጣት እንደሌለባቸው ቢጠይቁም፣ ዳኛው እንደማይስማሙ አስታውቀዋል።