Your browser doesn’t support HTML5
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኬንያና የአፍሪካ ጉብኝት የአፍሪካዊያንና የመሪዎቹ ችግሮችና ሥጋቶች ፊትለፊት የተነገሩበት እንደነበረና በመጭዎቹ ሣምንታትና ወራት ለውጦች ይመጣሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ታም ማሊኖውስኪ ገልፀዋል፡፡
ማሊኖውስኪ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ጉብኝት እጅግ ጠቃሚ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
“የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ እያየ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አጠገባቸው ተቀምጠው ሥራቸውን በመሥራታቸው ምክንያት የታሠሩ ጋዜጠኞች መለቀቅ አለባቸው ብለው አፍሪካ ኅብረት መድረክ ላይ ቆመው መናገራቸው እጅግ በጣም ግዙፍ ትርጉም ያለው ይመስለኛል” ብለዋል ታም ማሊኖውስኪ፡፡
የፀጥታ ጥያቄና የዴሞክራሲ ጉዳይ በቅርብ የሚያዩ መሆናቸውን የተናገሩት ማሊኖውስኪ ለምሣሌም የኬንያ መንግሥት አልሻባብን ሲያድን የሲቪሎችን ደኅንነት መንከባከብ፣ መብቶቻቸውን መጠበቅ እንዳለበት መግባባትና ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡
“ከራሣችን ልምድ እንደምንረዳው በመንግሥትና በመደበኛው ሰው በተለይ ደግሞ ከሙስሊም ማኅበረሰቦች ጋር መተማመን ከሌለ ይህንን ፍልሚያ እንደማናሸንፍ ስለምናውቅ ነው፡፡ ለራሣችን ደኅንነት ስንል መንግሥቱ እነዚህን ማኅበረሰቦች እንዲያዳምጥ፣ የተቃውሞ ድምፆችን እንዲሰማ፣ በማኅበረሰቦቹ ለሚነሱ አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች አግባብ የሆኑ ምላሾች እንዲሰጡ እንፈልጋለን፡፡” ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡