መንግሥት የሕግን የበላይነት የማስከበር ግዴታ አለበት - የኦነግ ቃል አቀባይ

ኦነግ

በትጥቅ ትግል መቀጠል የሚፈልግ ካለ መንግሥት በሰላም አሳምኖ ለመመለስ ጥረት ማድረግ አለበት፤ ካለበለዚያ “መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ግዴታ ስላለበት በወሰነበት መንገድ ሁኔታውን መቆጣጠር ይችላል” ብለዋል የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ እና የኦሮምያ ገዥ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ በመተማመን እና በመግባባት መንፈስ እንደሚሠሩ የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በትጥቅ ትግል መቀጠል የሚፈልግ ካለ መንግሥት በሰላም አሳምኖ ለመመለስ ጥረት ማድረግ አለበት፤ ካለበለዚያ “መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ግዴታ ስላለበት በወሰነበት መንገድ ሁኔታውን መቆጣጠር ይችላል” ብለዋል።

በኦዴፓና በኦነግ መካከል ሰሞኑን የተደረሰው ስምምነት አዲስ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ቶሌራ በግንባራቸውና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ሰኔ 1/2010 ዓ.ም. አሥመራ ላይ የተደረሰውን ባለሦስት ነጥብ ስምምነት በፈጠነ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።

የአሥመራው ስምምነት “ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን በሃገር ቤት እንዲቀጥል ማድረግ ማስቻል፤ ካለው መንግሥትና በተለይም ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ጋር የኦሮሞን ጉዳይ በተመለከተ መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር በጋራ የሚሠራበትን ሁኔታ በመደጋገፍ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ እንዲሁም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጋዮች ትግላቸውን በመንግሥት ድጋፍ የሚቀጥሉበትን ሁኔታ በመመካከርና በመነጋገር ማመቻቸት” እንደሆነ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ቃል አቀባይ አመልክተዋል።

ከኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ጋር የተደረገውን ቃለ-ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ከቪኦኤ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ