የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቶጎ መራጮች እጅግ ከፋፋይ ከሆነው ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ በኋላ ዛሬ ሰኞ በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል፡፡
ተቃዋሚዎች ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው ለአስርት ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየው የፕሬዚደንት ፎር ኛሲንግቤ ቤተሰብ አሁንም እንዲቀጥል መንገዱን አመቻችቷል ይላሉ፡፡
ትንሿን ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ለአራት አስርት ዓመታት የገዙትን አባታቸውን ኛሲንግቤ ኢያዴማን የተኩት ፕሬዚዳንት ፎር ኛሲንግቤ፣ ቶጎን ለ20 ዓመታት መርተዋል፡፡
ተቺዎች እንደሚሉት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው የኛሲንግቤን ቤተሰብ ስርወ መንግስት የሚያስቀጥል ነው፡፡
በባሕር ዳርቻ የምትገኘው የዋና ከተማዋ ሎሜ ነዋሪዎች፣ በቶጎ መሪ ሚና እና፣” መሪው ማን መሆን አለበት” በሚለው ምርጫ ዙሪያ ተለያይተዋል።
“አንድ ቤተሰብ ስልጣን ላይ ማየት ሰልችቶናል፡፡” የሚሉት ቀለም ቀቢው ኮምላን ጋቶ “የተወለድኩት እኤአ 1970 ስለሆነ በስልጣን ላይ ያለውን የኛሲንግቤን ቤተሰብ አውቃለሁ" ብለዋል፡፡
በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አያኦቪ ሶኹ "ለወጣቶች ምንም ዓይነት ስራ የለም፣ ተስፋ ቆርጠዋል፣ ሀገሪቱ በአግባቡ አልተመራችም እና የተዘረጋው ስርአት ሰልችቶናል፣ አሁን ግን ማንም ፍጹም ተግባራዊ ባልተደረጉ፣ በሚያማማሉና ባሸበረቁ ተስፋዎች አያታልለንም። አሁን እኛ በደንብ ነቅተናል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እኤአ ሚያዝያ19 በም ክር ቤቱ የጸደቀው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የፕሬዚዳንቱ ስልጣን ሥነ ስርዓታዊ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በተሻሻለው ሕገ መንግሥት መሠረት ፕሬዚዳንቱ አሁን የሚመረጠው በምክር ቤቱ እንጂ እንደቀድሞው በየአራት ዓመቱ በሕዝቡ አይመረጥም፡፡
በአዲሱ አወቃቀር ወሳኙን ስልጣን የሚይዘው የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ማለትም በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው ገዢው የሪፐብሊካን አንድነት ፓርቲ በዛሬው ምርጫ ካሸነፈ ፎር ኛሲንግቤ በሕገ መንግሥት ማሻሻያው የተቋቋመውን አዲስ ስልጣን መያዝ ይችላሉ፡፡
ተቺዎች ይህ መሆኑ ኛሲንግቤ የፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን ገደቦችን እንዲያልፉ ያስችላቸዋል ይላሉ፡፡