ታይም መጽሔት ስለ ወሲባዊ ወከባ እና ጥቃት ያነቁ የሚበዙት ሴቶች የሆኑ በርከት ያሉ ሰዎች የዘንድሮ የዓመቱ ሰው አድርጎ ሰይሟል።
የታይም መጽሔት ዋና አዘጋጅ ኤድዋርድ ፈለሶንታል ሲናገሩ ንቅናቄ እና ንቃት የቀሰቀሱት
“ዝምታ ሰባሪዎቹ” ናቸው ብለው፣ እንደ ሁልጊዜውም ታላላቅ ማኅበራዊ ለውጦች የሚጀምሩት በግለሰቦች በጀግንነት መነሳሳት እንደሆነ ገልፀዋል።
በዝምታ ሰባሪነት ታይም ከሰየማቸው መካከል የሆሊውዱን ባለከፍተኛ ሥልጣን ሃርቪ ዋይንስቲንን በወሲባዊ ጥቃት ተግባር የወነጀሉትንና ሌሎቹንም የተፈፀሙባቸውን ጥቃቶች ሀሽታግ/#/ ሚቱ /Hashtag #me too/ በተባለው የኢንተርኔት እንቅስቃሴ ይፋ ያደረጉ ይገኙበታል።
ታይም መጽሔት በየዓመቱ በሚመርጠው የዓመቱ ሰው ስያሜ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሁለተኛነት የቻይና ፕሬዚደንት ሺ ዢን ፒንግ ደግሞ በሦስተኝነት ተከትለዋል።
የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን የሳውዲ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን የዩናይትድ ስቴትሱ ልዩ ዓቃቤ ሕግ ሮበርት ሞለርም አሉበት።
ዘረኝነትንና የፖሊሶች የጭካኔ አያያዝ ለሀገርቀፍ ተቃውሞ ያንቀሳቀሰው የቀድሞ የአሜሪካ ፉትቦል ተጫዋች ኮሊን ኬፓርኒክም የዓመቱ ሰው ዝርዝር ውስጥ ገብቷል።
ታይም መጽሔት በዓመት ውስጥ ትልቅ ዜና የፈጠረ ግለሰብ ወይም ቡድን፣ የዓመቱ ሰው ብሎ ሲያደንቅ ዘንድሮ ዘጠና አንደኛ ዓመቱ ነው።