ትግራይ ክልል ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ክፍት መሆኑን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ትናንት [ሐሙስ] መቐለ ከተማ በተካሄደው የቱሪዝም ማስጀመሪያ መርኃግብር ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ደ’ኤታ ስለሺ ግርማ ቅርሶችና የማመላለሻን ጨምሮ አገልግሎት ሰጭዎች ዝግጁ መሆናቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጀመሩ ለክልሉ ምጣኔኃብት ከሚሰጠው ቀጥተኛ ጥቅም በተጨማሪ ሰላሙን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ዘርፉን በሚገባ ለማንቀሳቀስ ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ለባለሞያዎች ሥልጠናና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በኮቪድ 19፣ ቀጥሎም በጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የትግራይ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጀመሩ በዘርፉ በተሠማሩ የክልሉ ነዋሪዎች ዘንድም ተስፋ መፈንጠቁን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመሩት "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት አካል የሆነው የትግራይ ክልል ገርዓልታ የመዝናኛ ሎጅ ግንባታ እንቅስቃሴ በሐውዜን አካባቢ መጀመሩንም አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
የጉዞ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ያወጡ ሃገሮች አሁን ያንን አቋማቸውን እንዲከልሱ ለማድረግ የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሚቀጥል ሚኒስትር ደ’ኤታ ስለሺ ገልፀዋል።
በአኵስም ከተማ የሚገኘው የአይሮፕላን ጣቢያ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ስለደረሰበት ጥገና እየተደረገለት መሆኑ ታውቋል።