የትግራይ ክልል መሪ ኃይሎቻቸው አስመራ ላይ ሮኬት መተኮሳቸውን ተናገሩ

Dr. Debretsion Gebremichael

ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ላይ ኃይሎቻቸው ሚሳይል መተኮሳቸውን የትግራይ ክልል መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካዔል አረጋገጡ።"ገና ይቀጥላል፥ ማናቸውም ወታደራዊ ዒላማ ላይ እንተኩሳለን" ሲሉም ዝተዋል።

ትናንት ቅዳሜ የተተኮሰው ስንት ሚሳይል እንደሆነ ያልገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን ዒላማ ያደረግነው አስመራ ከተማን ብቻ ነው ብለዋል።

ይህ የትግራይ ክልል መሪው መግለጫ በክልላቸው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር እየተካሄደ ያለው ውጊያ ወደ አጎራባች ኤርትራም ዘልቆ እየተባባሰ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተመልክቷል።

ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች በበኩላቸው የትግራይ መሪዎች ጥቃት እንደሚያደርሱ ዛቻ ባሰሙ ጥቂት ሰዓታት ተከትሎ አስመራ ላይ ሶስት ሮኬቶች መተኮሳቸውን ተናግረዋል። ሮኬቶቹ ዒላማ ያደረጉት አውሮፕላን ጣቢያውን ሳይሆን እንዳልቀረ የተገለጸ ሲሆን በጥቃቱምን ያህል ጉዳት እንደደረሰም ሆነ የሰው ህይወት ጠፍቶ እንደሆን የተገኘ መረጃ የለም።

የትግራይ ክልል አስተዳዳሪው ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችን የሚረዱ ወታደሮች እየላከች ነው ሲሉ መወንጀላቸው እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ ክሱን ማስተባበላቸው ይታወሳል። ስለሚሳይል ጥቃቱ ከኤርትራ በኩል እስካሁን የተሰጠ አስተያየት አልተገኘም።

የትግራይ ክልል ኃይሎች ዓርብ ሊሊት በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ባህር ዳር እና ጎንደር አውሮፕላን ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ ሮኬቶች መተኮሳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥትም የክልሉም መንግሥት አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት በትግራይ ቴሌቭዥን ባወጣው መግለጫ የሚፈጸምብን ጥቃት ካልቆመ ጥቃት መሰንዘራችንን እንቀጥላለን ብሏል።

ባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ በተተኮሱት ሮኬቶች አውሮፕላን ጣቢያው አካባቢ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።