ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ከፖለቲካ ጭቆና ለማምለጥ፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ እና ከግጭት ለመሸሽ ትውልድ አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን እና በስደት ውስጥ ለብዙ አካላዊ፣ ዲጂታል እና ሕጋዊ ስጋቶች መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን አስታውቋል።
የተቋሙ መርማሪ አይሬን ካሃን ለመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ባቀረቡት ሪፖርት "አምባገነንነት እየጎለበተ በሄዱባቸው የዲሞክራሲ አገሮች" ለገለልተኛ እና መንግስትን ለሚተቹ ሚዲያዎች ያለው ምህዳር እየጠበበ በመሄዱ የሚሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።
ካሃን አክለው በአሁኑ ሰዓት፣ ከአለም ህዝብ አንድ ሦስተኛው በላይ በሚኖሩባቸው አገራት የሚገኙ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ብዝኃነት ያላቸው፣ ዲሞክራሲን የሚደግፉ እና ስልጣን ላይ ያሉትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሚዲያዎች ጠፍተዋል ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ተገድበዋል ብለዋል።
ቀደም ሲል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሃፊ ሆነው ያገለገሉት ካሃን፣ በስደት ያሉ ጋዜጠኞችም ከትውልድ አገራቸው በእራሳቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ በሚደርስ ማስፈራሪያ ምክንያት እና በስደት ባሉበት አገርም መኖር የሚያችላቸው ህጋዊ ሁኔታ እና የስራ ፈቃድ ስለማያገኙ፣ አብዛኛውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ አብራርተዋል።
"ብዙ ጋዜጠኞች ለእራሳቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት በመፍራት እና በባዕድ አገር የመኖርን ብዙ ፈተናዎች ለማሸነፍ የሚያስችላቸው ገንዘብ ለማግኘት ቀስ በቀስ ሙያቸውን ይተዋሉ" ያሉት ካሃን፣ በዚህ ምክንያት ስደት ወሳኝ ድምጾችን ዝም የማፈኛ እና ፕሬስ ላይ ሳንሱር የማድረጊያ ሌላ መንገድ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አመልክተዋል።