በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ 840,060 የሚሆኑ በኮቫክስ አማካኝነት የሚለገሱ የመጀመሪያ ዙር የፋይዘር ክትባቶች ዛሬ ቦሌ አየር ማረፊያ መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ከለገሰችው ጋር በአንድነት የሃገሪቱን ልገሳ ወደ 7 ሚሊየን እንደሚያስጠጋው መግለጫው አስፍሯል፡፡ ይህ የክትባት ድጋፍ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሆነ የክትባት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ ያለመና በተለዋጭ ከኢትዮጵያ በኩል ምንም ዓይነት የሚጠበቅ ነገር ሳይኖር የተደረገ ነው ሲል ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር ሃገር አቀፍ የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ከሁለት ሳምንታት በፊት የጀመረች ሲሆን ይህ ድጋፍም ዘመቻውን ለማገዝ ትልቅ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ 1.1 ቢሊየን የሚደርስ የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ በዓለም ዙሪያ ለማዳረስ ቃል የገባች ሲሆን እስካሁን ድረስም 400 ሚሊየን የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለ110 ሃገራት ማዳረሷ ታውቋል፡፡
ሃገሪቱ ጋቪ በተሰኘው የክትባት ገበያ ቃልኪዳን አማካኝነትም የፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በአለም አቀፍ ደርጃ ኮቪድ-19ን ለመዋጋት የገቡትን ቃል በማክበር ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በአንድነት መስራታችንን እንቀጥላለን ሲል መገልጫው አስታውቋል፡፡