አሜሪካውያን፣ ከ22 ዓመት በፊት፣ እ.እ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 የደረሰውን አሠቃቂ የሽብር ጥቃት ለማሰብ፣ ዛሬ ሰኞ፣ በአገሪቱ የመታሰቢያ ስፍራዎች እና በሌሎችም ቦታዎች ተሰባስበዋል።
በየከተሞቹ የመታሰቢያ ሐውልቶች፣ በእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያዎች፣ በማዘጋጃ ቤት አዳራሾች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የተገኙት አሜሪካውያን፣ ዕለቱን ሲዘክሩ ውለዋል፡፡
ጥቃት በተፈጸመባቸው በኒው ዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል፣ ፔንታጎንና ሻንክስቪል ፔንስልቬንያ፣ እንዲሁም በሌሎችም ቦታዎች፣ የመታሰቢያ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከሠራዊቱ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ጋራ በአንከሬጅ፣ አላስካ ወታደራዊ ጦር ሰፈር በተካሔደው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
የፕሬዚዳንቱ የአላስካ ጉብኝት፣ በመስከረም 11 ቀን የተፈጸመው የሽብር ጥቃት፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጽእኖ አስከትሎ እንደነበር ለማስታወስ ነው፤ ተብሏል።
በዕለቱ በተጠለፉ አውሮፕላኖች በደረሱ የሽብር ጥቃቶች፣ ወደ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ጥቃቱ፣ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን እንድትከልስ ሲያስገድዳት፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ስጋቶችንም መልክ መቀየሩ ተመልክቷል፡