ባለፈው ዓመት በጋዛ ግጭት መሞታቸው ከተረጋገጠ ሰዎች መካከል 70% የሚጠጉት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ዛሬ ዓርብ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ዘገባ አመልክቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ “ይህ የዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ ህግ መሰረታዊ መርሆችን ስልታዊ በሆነ መንገድ የጣሰ ነው” ሲልም ድርጊቱን አውግዟል፡፡
የሟቾቹ ቁጥር፣ ከአንድ ዓመት በፊት በጀመረው የእስራኤል ሀማስ ጦርነት፣ የመጀመሪያዎቹን ሰባት ወራት የሚሸፍን መሆኑን ባለ 32 ገጹ የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ አመልክቷል፡፡
በዚህ ሰባት ወር ጊዜ ውስጥ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ የተረጋገጠው የሟቾች ቁጥር 8 ሺሕ 119 ሲሆን፣ ይህ የፍልስጤም የጤና ባለሥልጣናት በ13 ወራት ግጭት ከ43ሺሕ በላይ ነው ሲሉ ከጠቀሱት ቁጥር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የድርጅቱ ዘገባ በጦርነቱ ከተገደሉት መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ህጻናትና ሴቶች ናቸው የሚለውን የጤና ባለሥልጣናቱን ዘገባ ይደግፋል፡፡
የድርጅቱ ዘገባ “የዓለም አቀፍ ህግን ጥሰዋል ሊባሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ የፍትህ ምርመራ እንደሚያስፈልግ እና ማስረጃዎች ለተጠያቂነት ሲባል መጠበቅ እንደሚገባቸው” በመጠቆም አጽንኦት ሰጥቷል።
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2023 በደቡብ እስራኤል 1ሺሕ 200 የሚጠጉ ሰዎችን የገደለው እና ከ250 በላይ ሰዎችን አግቶ የወሰደውን የሃማስ ጥቃት ተከትሎ የአጸፋ ርምጃ መወሰድ መጀመሯን የገለጸችው እስራኤል የሰለማዊ ዜጎችን ጉዳት ለመቀነስ እየሞከረች መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሀማስ ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀመበት ነው ስትልም እስራኤል ሀማስን ትከሳለች፡፡
ጥቃቱ “ተመጣጣኝ አለመሆኑን” በገለጸው የድርጅቱ ዘገባ ከተረጋገጡ ሟቾች መካከል፣ ትንሹ ተጎጂ የአንድ ቀን ወንድ ልጅ ሲሆን፣ ትልቋ ደግሞ የ97 ዓመት ባልቴት እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ ዘገባው አክሎም ይህም በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያስከተለውን ሰፊ ተጽእኖ አጉልቶ ያሳያል ብሏል፡፡
ዘገባው በእስራኤል በተካሄዱ 88 ከመቶ በሚሆኑ ጥቃቶች ከአምስት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች የተገደሉ መሆኑን ገልጾ ከተጎጂዎች መካከል 44 ከመቶ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን አመልክቷል፡፡