በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ የሚገኘው ትልቁ የኢፌል ታወር (ቱር ኢፌል) ሐውልት አድማ በመቱ ሠራተኞች ምክንያት ዛሬ ረቡዕ ለጉብኝዎች ዝግ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሀውልቱ የተዘጋበት ወቅት የፓሪስ ሃውልቱ ፈጣሪው ጉስታቭ ኢፌል ከሞተ 100 አመት ያስቆጠረበት ቀን በመሆኑ እለቱን የተለየ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
የኢፌል ታወር ቃል አቀባይ ቱሪስቶች አሁንም የሐውልቱን ታችኛውን ክፍል ብቻ መመልከት የሚችሉ መሆኑን ጠቅሰው ላልተወሰነ ጊዜ ግን 324 ሜትር (1,063 ጫማ) ከፍታ ወዳለው ሐውልት ጫፍ መውጣት እንደማይችሉ አስታውቃወዋል፡፡
የሠራተኞቹ አድማ የተመታው 134 ዓመታትን ያስቆጠረው የመታሰቢያ ሐውልት ባለቤት ከሆነችው ከፓሪስ ከተማ ጋር የኮንትራት ድርድር ከመጀመሩ በፊት ነው ሲሉም ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ፈቃድ የሌላቸውና ስማቸው ያልተገለጸው ቃል አቀባይ መናገራቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የሠራተኞቹ ኅብረት ተወካዮች ወዲያውኑ ምላሽ ያልሰጡ ሲሆን፣ አድማው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይም ግልጽ አይደለም ሲል ዘገባው አመልክቷል፡፡
በዓለም ላይ በብዛት ከሚጎበኙ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው የኢፌል ታወር በዓመት 365 ቀናት ክፍት ሲሆን እኤአ በ2024 በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ የዓመቱ ክፍለ ጊዜ በየቀኑ ወደ 20ሺ ጎብኝዎች እንደሚመለከቱት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
አስቀድሞ በተያዘው እቅድ መሠረት ዛሬ ረቡዕ ምሽቱን እኤአ ታህሳስ 27 ቀን 1923፣ ጉስታቭ ኢፌል የሞተበትን እለት የሚዘክር ልዩ የሙዚቃ ትርኢት በማህበራዊ አውታረ መረቦች እና በፈረንሳይ ቴሌቪዥን ሊለቀቅ ታስቦ እንደነበርም ቃል አቀባይዋ ገልጸዋል፡፡