በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ግዛት የ14 ዓመት ታዳጊ አራት ሰዎችን በመግደል ተከሰሰ

  • ቪኦኤ ዜና
የሕክምና ሄሊኮፕተር በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ግዛት፣ ከአትላንታ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አፓላቺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ታይቷል

የሕክምና ሄሊኮፕተር በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ግዛት፣ ከአትላንታ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አፓላቺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ታይቷል

በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ግዛት፣ ከአትላንታ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አፓላቺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት የ14 ዓመት ተማሪዎችን እና ሁለት መምህራንን የገደለው ታዳጊ በግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

ታዳጊው ትላንት ረቡዕ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በተከፈተው ተኩስ ሌሎች ስምንት ተማሪዎች እና አንድ አስተማሪ ማቁሰሉንም ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በትምህርት ቤት ላይ ተኩስ እንደሚከፍት በመዛት በድረ-ገጾች ላይ ይፅፍ እንደነበር የጆርጂያ ፖሊስ መረጃ ደርሶት በወቅቱ የ13 አመት ልጅ የነበረውን ታዳጊ አነጋግረውት የነበረ ሲሆን፣ ፖሊስ በቂ ማስረጃ ባለማግኘቱ በነፃ ተለቋል።

የጆርጂያ ፓሊስ ተማሪውን እና አባቱን ባነጋገረበት ወቅት፣ አባቱ ቤታቸው ውስጥ የአደን ጠመንጃዎች እንዳሏቸው፣ ሆኖም ታዳጊው ያለ ወላጅ ቁጥጥር ሊደርስባቸው እንደማይችል ተናግረው ነበር። ታዲጊውም በድረ-ገፅ ላይ ማስፈራሪያ መፃፉን አላመነም።

አሁን 14 ዓመት የሞላው ታዳጊ ጠመንጃ ይዞ ወደ የሒሳብ ትምሕርት ክፍል ለመግባት ሲሞክር የክፍል ጓደኞቹ በሩን ሊከፍቱለት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መተኮስ እንደጀመረ፣ የክፍል ጓደኛው ለይላ ሳያራት ተናግራለች።

ተማሪው የያዘውን ጠመንጃ ከየት እንዳገኘው እና እንዴት ወደ 1ሺህ 900 ተማሪዎች ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት ሊያስገባ እንደቻለ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።