የኑሮ ውድነት ያማረራቸው ኬንያውያን ሰልፍ ወጡ

የኑሮ ውድነት እጅግ በመናሩ ምክንያት ተማረው ሰልፍ በወጡ ኬንያውያን ላይ ፖሊስ አሰለቃሽ ጭስ ሲተኩስ

የኑሮ ውድነት እጅግ በመናሩ ምክንያት ተማረው ሰልፍ በወጡ ኬንያውያን ላይ ፖሊስ አሰለቃሽ ጭስ ሲተኩስ

የኑሮ ውድነት እጅግ በመናሩ ምክንያት ተማረው ሰልፍ በወጡ ኬንያውያን ላይ ፖሊስ አሰለቃሽ ጭስ ሲተኩስ ሰልፈኞቹ በአጸፋው ድንጋይ ወርውረዋል።

በተቃዋሚ ፓርቲ በተጠራው ሰልፍ የናይሮቢና ቢያንስ አንድ ሌላ ከተማ ነዋሪዎች መሳተፋቸው ሲታወቅ፣ ፕሬዚዳንት ሩቶ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ፖሊስ ለስልፉ ፈቃድ ያልሰጠና መንግሥትም ዕርምጃ እንደሚወስድ ያስጠነቀቀ ቢሆንም የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ግን ሰልፉ በታቀደለት መሠረት እንዲካሄድ ጥሪ አድርገዋል።

“ኬንያውያን በብዛት ወጥተው በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ነገሮች እንዳላስደሰቷቸው ማሳወቅ አለባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል ኦዲንጋ ለደጋፊዎቻቸው ዕሁድ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት።

በማዕከላዊ ናይሮቢና በሌሎች የከተማዋ ሥፍራዎች በመንግሥት ቢሮዎች አካባቢ በተሰባሰቡ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ተኩሷል።

በህግ መወሰኛ ም/ቤቱ የአነስተኛ ቁጥር መቀመጫ ያለው ፓርቲ መሪ የሆኑት ስቲዋርት ማድዛዮን ጨምሮ ሁለት የምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ሰልፈኞች በፖሊስ መያዛቸውን የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችና የኦዲንጋ ጠንካራ ደጋፊዎች በብዛት በሚገኙበት ኪቤራ በተባለው የናይሮቢ ክፍል ያሉ ሰልፈኞች ጎማ ሲያቃጥሉ ፖሊስ በውሃ በትኗቸዋል።

በመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ውድነት፣ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ሺሊንግ ከዶላር አንጻር እጀግ በመውረዱ እና በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት ኬንያውያን ኑሮ ተጭኗቸዋል።