የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች አስከሬኖች ናቸው ብሎ እንደሚያምን የታንዛኒያ ፖሊስ የጠረጠራቸውን 13 አስከሬኖች መንገድ ላይ ወዳድቀው ማግኘቱን አስታወቀ።
ዋሺንግተን ዲሲ —
የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች አስከሬኖች ናቸው ብሎ እንደሚያምን የታንዛኒያ ፖሊስ የጠረጠራቸውን 13 አስከሬኖች መንገድ ላይ ወዳድቀው ማግኘቱን አስታወቀ።
አስከሬኖቹ መንገድ ላይ የተገኑት ሞሮጎሮ በሚባል የምሥራቃዊ ታንዛኒያ አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።
አንድ ሕፃንን ጨምሮ ሌሎች ሰባት ሰዎችን በአቅራቢያው በሚገኝ ጫካ ውስጥ በሕይወት ማግኘቱን የሃገሪቱ ፖሊስ አክሎ አመልክቷል።
በሕይወት የተገኙት ሰዎች የጤና ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንመ ተናግሯል ፖሊስ።
ሰዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ በከባድ ተሽከርካሪ እየተጓዙ እንደነበረ፣ አሽከርካሪው ታንዛኒያ የተገኙበት አካባቢ እንደደረሰ አራግፏቸው መሄዱንና የቀበሌው ሰዎች ሁኔታውን ለፖሊስ ማመልከታቸውን የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ተናግረዋል።
ሰዎቹን አሽከርካሪው ያራገፋቸው ጊዜ ሁሉም በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ለጊዜው አልታወቀም።
አሳፍሯቸው የነበረው የልነት መኪና አስከሬኖቹ በተጣሉበት አካባቢ ያለአሽከርካሪው ቆሞ መገኘቱም ታውቋል።
የተነሱት ከኢትዮጵይ መሆኑን ለቪኦኤ ስዊሂሊ አገልግሎት የተናገረ አንድ በሕይወት የተረፈና ሆስፒታል የሚገኝ ተሣፋሪ የተጫኑበት ተሽከርካሪ የተጨናነቀ እንደነበረና አየር በውስጡ እንዳልነበረ ገልጿል።
ፖሊስ ሁኔታውን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።