በድጋሚ የታደሰ
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ዛሬ፣ በታንዛኒያ የሰላም ንግግር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ ለሰላም ንግግሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮች በስፍራው እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የሰላም ንግግሩ እንደሚደረግ ቢያረጋግጡም፣ በትክክል የት ቦታ እንደሚገናኙ ተነጋጋሪ ወገኖችም ኾኑ የታንዛንያ ባለሥልጣናት፣ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ መቆጠባቸውን ሮይተርስ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥትን ልኡክ የሚመሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን መኾናቸውን፣ ስለጉዳዩ የሚያውቁና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል። ንግግሩ የሚካሔደው በዛንዚባር ደሴት ላይ እንደሚኾን ከምንጮቹ አንዱ ለሮይተርስ ጠቁመዋል፡፡
በቅርብ ዓመታት ውስጥ፣ በኦሮሚያ ክልል በመቶ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የኾነውን ግጭት ለማቆም ውይይት እንደሚጀምሩ የጠቆመው የሮይተርስ ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 11 ክልሎች ትልቁ የኾነውና ዋና ከተማዋን ዐዲስ አበባን በከበበው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ዐማፂ ቡድን፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ ሲዋጋ ዐሥርት ዓመታት ማስቆጠሩን ያትታል። ይህ ታጣቂ ቡድን፣ መንግሥት በአገሪቱ ትልቁ የኾነውን የኦሮሞ ብሔርን ያገለለ ነው፤ በሚል ክሥ ያሰማል።
ባለፈው ጥቅምት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሔድ የነበረውና በ10ሺሕ የተቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት በሰላም ስምምነት ከቆመ በኋላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከገጠሙት የጸጥታ መታወኮች አንዱ በኦሮሚያ ክልል ያለው የማያባራ ግጭት ነው። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ፓርቲ አቋቁሞ ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ተገንጥሎ የወጣ ቡድን መኾኑን ሮይተርስ በዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ ለብዙ ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሒድ የቆየው ኦነግ አመራሮች፣ በተለያየ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል። በዚኽ ወቅት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ከግንባሩ ተገንጥሎ የወጣ ቡድን መኾኑን አስታውቆ ነበር። ይህ ታጣቂ ቡድን፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከመንግሥት ወታደሮች ጋራ ውጊያ እያካሔደ እንደሚገኝ፣ የቡድኑ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ በተለያየ ወቅት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸው ነበር።
SEE ALSO: ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋራ ይጀመራል የተባለው ድርድር ተስፋ እንደፈነጠቀላቸው ነዋሪዎች ተናገሩለሁለት ዓመታት የዘለቀውና በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከስድስት ወራት በኋላ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል ስያሜ ከህወሓት ጋራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈረጀ።ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባካሔደው ልዩ ስብሰባ፤ ህወሓት ከሽብር ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ አኹንም ኢትዮጵያ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት ነው።
በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች፤ ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ደግሞ የዐማራ ተወላጆችን ለይቶ ያጠቃል፤ ከመኖሪያ ቀዬአቸውም ያፈናቅላል፤ በሚል ክሥ ይቀርብበታል። ቡድኑ በተደጋጋሚ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳልፈጸመ ቢያስተባብልም፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ግን፣ የጅምላ ግድያ እና ማፈናቀል፣ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራ ታጣቂ ቡድን እንደተፈጸመባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሻል ባለፈው ወር በአወጣው ሪፖርት፣ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ፣ በአንድ ቀን ከ400 በላይ የዐማራ ተወላጅ ሰላማውያን ተጨፍጭፈው መገደላቸውንና ለግድያውም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ ማድረጋቸውን፣ ከጥቃት የተረፉ እማኞቹን ጠቅሶ ነበር። በዐማራ ብሔር ተወላጆች ላይ፣ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመውና “አሠቃቂ” ብሎ የገለጸው ግድያ እንዲመረመርም የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጠይቆ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰላም ስምምነት እንዲቋጭ “ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል” ለተባሉ አካላት “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ቃል ባለፈው እሑድ፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ በተዘጋጀ የምስጋና እና የዕውቅና ዝግጅት፣ መንግሥታቸው “ኦነግ ሸኔ” ካሉት ታጣቂ ቡድን ጋራ በታንዛንያ ድርድር እንደሚጀመር በይፋ አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት ድርጅቱን “ሸኔ” ብሎ ከመጥራት እንዲቆጠብ ያሳሰበው ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት መዘጋጀቱን አረጋግጧል።