ሩሲያ ዓርብ በምታስተናግደው ቀጠናዊ ስብሰባ ላይ በታሊባን ከምትተዳደረው አፍጋኒስታን ጋር በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ፀረ-ሽብርተኝነት እንዲሁም ሕገወጥ የእፅ ዝውውሮች ዙሪያ መስራት በሚቻልበት እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ሩሲያ አፍጋኒስታንን በተመለከተ ለስድስተኛ ዙር በምታካሂደው በዚህ ጉባዔ ላይ፣ የታሊባን የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አሚር ካሃን ሙጣቂ "ዋና እንግዳ" ሆነው እንደሚገኙ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀብይ ማሪያ ዛካሮቫ አስታውቀዋል።
ሩሲያ ተከታታይ ጉባዔውን በእ.አ.አ በ2017 ከጀመረች ወዲህ፣ በድህነት እና በጦርነት የምትታመሰው አፍጋኒስታን ያሉባት ችግሮች ቋሚ መወያያ መድረክ ሆኗል።
በስብሰባው ላይ ከቻይና፣ ህንድ፣ ኢራን፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ፓኪስታን፣ ታጃኪስታን፣ ቱክርሜኒስታን እና ኡዝቤኪስታን የተውጣጡ ተወካዮች እንደሚገኙ ዛካሮቫ ረቡዕ ዕለት በሩሲያ መዲና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።