የቻይናን ተስፋፊነት ለመግታት ከአሜሪካ ጋራ እንደሚሠሩ የታይዋን ፕሬዝደንት አስታወቁ

ፎቶ ፋይል፦ የታይዋን ፕሬዝደንትነት ላይ ቺንግ ተ

ከሳምንት በፊት በታይዋን በፕሬዝደንትነት የተመረጡት ላይ ቺንግ ተ፣ “የፈላጭ ቆራጮችን መስፋፋት” ለመግታት ከአሜሪካ ጋራ እንደሚሠሩ በሃገሪቱ ጉብኝት ላይ ለሚገኙት የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ተናግረዋል።

የፕሬዝደንቱ አስተያየት የመጣው ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ ልምምድ ባደረገች ቀናት ውስጥ ነው።

ከአሜሪካ ሴኔት ከሁለቱም ፓርቲዎች ከተውጣጣው የልዑካን ቡድን ጋራ ዛሬ ረቡዕ የተወያዩት ላይ ቺንግ ተ፣ አሜሪካ ድጋፏን እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ከሳምንት በፊት ፕሬዝደንቱ ቃለ ማሃላ በፈፀሙ በቀናት ውስጥ፣ ቻይና የጦር አውሮፕላኖችና መርከቦች የተሳተፉበት ከፍተኛ የጦር ልምምድ በታይዋን ዙሪያ አድርጋለች፡፡ ፕሬዝደንቱ ታይዋን ነፃ ሃገር መሆኗን በመናገራቸው የተደረገ “የቅጣት” ብላ የገለፀችው ወታደራዊ ልልምምድ መሆኑን ቻይና አስታውቃለች።

“ከሃጅ” እና “ለሠላምና መረጋጋት ፀር” ስትል ቻይና ላይ ቺንግ ተን ትገልጻቸዋለች፡፡

የጉብኝት ቡድኑ ዓባል የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲው ሴናተር ታሚ ደክዎርዝ፣ “ከታይዋን ጎን ሁሌም እንደምንቆም ልታምኑ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።