በሶሪያ የርስ በርሱ ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ ማርች 15፣ ልክ አስረኛ ዓመቱ ነው፡፡ በብዙዎቹ የሶሪያ ግዛቶች የሶሪያው መንግሥት ፕሬዚዳንት ባሽር አል አሳድ ባለ ድል ሆነው ይታያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ግን የአማጽያኑ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው እድሊብ ተቃውሞው እንደበረታ ነው፡፡ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሶሪያውያንም በጦርነቱ ታግተው ይገኛሉ፡፡
በሶሪያ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የርስ በርሱ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ፈጅቷል፡፡ በሚሊዮኖችን የሚቆጠሩትን አፈናቅሏል፣ የአያሌዎችን ህይወት አመሰቃቅሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ባሽር አል አሳድ ሊገባደድ የተቃረበውን ጦርነት በድል ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ደግሞ እዚህም እዚያም የተበታተነውን ውጊያ እየጠቀሱ፣ የተቃዋሚዎቹ ጠንካራ ይዞታ የሆነውችን ኢድልብንና፣ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ አካባቢዎችን እያነሱ፣ ጦርነቱ “ተዳፍኗል” ይላሉ፡፡ ወደ 17.5 ሚሊዮን ከሚጠጋው የሶሪያ ህዝብ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋው ህዝብ የሚኖረው በእነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡
እድሊብ ከተማ ውስጥ የፕሬዚዳንት አሳድን መንግሥት በመቃወም፣ በየሳምንቱ የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል፡፡ ተቃዋሚዎቹ አብዮታችን ይቀጥላል ይላሉ፡፡
ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አንዋር የሱፍ እንዲህ ብለዋል
“ዛሬም የምንጠይቀው የዛሬ አስር ዓመት በ2011 እንጠይቀው የነበረውን ጥያቄ ነው፡፡ የአገዛዙ የደህንነት ኃላፊ እስካልተወገደ ድረስ ወደ ቤታችን መመለስ አንፈልግም፡፡ ከቤታችን ተገደን መውጣታችን እንኳ ግድ አይሰጠንም፡፡”
በእድሊብ ግዛት የሚኖሩት ብዙዎቹ ሶርያውያን፣ በፕሬዚዳንት አሳድ አገዛዝ ስር ሆነው፣ ፈጽሞ በሰላም ሊኖሩ እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
በዙዎቹ አካባቢዎች፣ በሃይ ኣት ታኻሪር አል ሻም ወይም በምህጻረ ቃሉ HTS፣ በሚባለው ቡድን ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ቡድኑ ራሱን የሚገልጸው በሶሪያ ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖች ድምር አድርጎ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ግን፣ HTS ራሱ፣ ቀደም ሲል ከአልቃይዳ ጋር በነበረው ግንኙነት፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀ አካል ነው፡፡
ቡድኑ በግልጽ ያስቀመጠው አቋም፣ የፕሬዚዳትን አል አሳድን መንግሥት ማስወገድና የሳቸውንም ተባባሪ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ኃይሎች ከሶሪያ ጠራርጎ ማስወጣት ነው፡፡
የHTS ቃል አቀባይ አቡ ካሊድ አልሻኻሚ እንዲህ ብለዋል
“ እኛ አብዮት ነን፡፡ የምንፈልገው ይህ ወንጀለኛ ስብስብ ተባሮ እንዲወጣ ነው፡፡ የአሳድ ወታደራዊ ኃይል፣ የኢራን ሚሊሻዎችና አገራችንን የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኃይሎች ከሶሪያ ተጠራርገው እንዲወጡ እንፈልጋለን፡፡”
በሶሪያ ውስጥ ያሉ ሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎችንም በመደገፍም በኩል ቱርክ የራሷን ድርሻ ትጫወታለች፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት በሶሪያ ወደፊት ሊኖር የሚችለው ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካ ለውጥ የሚወሰነው በተቃዋሚዎች አንጻር ቱርክ፣ በአሳድ ደጋፊዎች በኩል ደግሞ ሩሲያና ኢራን በሚያደርጉት ነገር የሚወሰን ይሆናል ይላሉ፡፡
አሁን እንዳለው ሁኔታ ከሆነ፣ ሙሉ ጦርነት የሚካሄድ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ቱርክ ድንበር በመጉረፍ፣ ሊያጠለቀልቋት ይችላሉ፡፡ አሁን ራሱ፣ ቱርክ ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያውያን ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው፡፡ ስለዚህ፣ ቱርክ ለሌላ ተጨማሪ ስደተኛ ድንበሯን ከመክፈት፣ አሳድን ራሱ ባሉበት መታገሉን ትመርጣለች፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የእድሊብ ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በረሃብ እየተጠቁና መጠለያ አልባ በሆኑበት ሁኔታ ውስጥ፣ ነገሮችን በፊት እንደነበሩት ማስቀጠሉ የማይታሰብ ነው፡፡
የእድሊብ ነዋሪ የሆኑ ሻሃዲ ሾያብ እንዲህ ይላሉ
“ሁሉንም ነገር አጥተናል፡፡ ሁሉንም ነገር፡፡ ኢኮኖሚያችንን፣ ትምህርታችንን፣ እንዲሁም የፍትህ ሥርዓቱ ሁሉ ሳይቀር ወድሟል፡፡
ሾያብ ጨምረው እንዲህ አሉ፣ “የዛሬ አስር ዓመት የነበረው አመጽና ጥያቄ፣ ዴሞክራሲና ፍትህን መጠየቅ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን አሉ ሾያብ
“አካባቢውን ዞር ዞር ብላችሁ ብትመለከቱ ሰዎች በጣም ከመቸገራቸው የተነሳ ህይወታቸውን እንኳ ማሰንበት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስላሉ፡፡”
የቪኦኤ ዘጋቢዎች ሄዘር እና ሻዲ ተርክ ከእድሊብ ሶሪያ ከላኩት ዘገባ የተወሰደ፡፡